የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች በካምባ ዙሪያ ወረዳ ዲንጋሞ ቀበሌ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና በክርስቲያን ኤይድ ትብብር ግንባታው ሊጠናቀቅ የተቃረበውን የዲንጋሞ አነስተኛ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ኅዳር 28/2017 ዓ/ም የመስክ ምልከታ አካሂደዋል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት በኃይሉ መርደኪዮስ (ተባባሪ ፕ/ር) እንደገለጹት የዲንጋሞ ቀበሌን የመብራት ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል አነስተኛ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተገንብቶ ኃይል ማመንጨት መጀመሩን አስመልክቶ በቀጣይ ሊከናወኑ በሚገቡ ጉዳዮች ላይ ምክክር ለማካሄድ የመስክ ምልከታው ተደርጓል፡፡ ፕሮጀክቱ ማኅበረሰቡን በልማት ያሳተፈ የትክክለኛ የማኅበረሰብ ጉድኝት ምሳሌ እንዲሁም ከሀገር ባሻገር በአፍሪካ ሀገራት ለሚገኙ የዘርፉ ተመራማሪዎች የተሻለ ልምድና ተሞክሮ መቅሰም የሚያስችል መሆኑን ም/ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡
የማኅበረሰብ ጉድኝትና የኢንደስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ በበኩላቸው የአካባቢው ማኅበረሰብ በዩኒቨርሲቲው ላይ ከጣለው ተስፋ አንጻር ፕሮጀክቱ እዚህ ደረጃ መድረሱ የሚያስደስት መሆኑን ተናግረው የዩኒቨርሲቲው ባለሙያዎች፣ አመራሮችና የአካባቢው ማኅበረሰብ ለውጤታማነቱ ላሳዩት ትብብርና ርብርብ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂ ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ያሊሾ ግርማ ታዳሽ ኃይል ለሰው ልጅ ዘመናዊ አኗኗርና ለቴክኖሎጂ እድገት መሠረት ቢሆንም እንደ ሀገር ያለንን ሀብት ከመጠቀም አንጻር ዘርፈ ብዙ ተግባራት የሚጠበቁ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎትና አቅርቦት የተጣጣመ አለመሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ ዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰቡን ችግር በመለየት የኃይል ተጠቃሚ መሆን የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የማዕከሉ ተመራማሪና የፕሮጀክቱ ማኔጀር ኢ/ር በየነ ፈዬ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ 15 ኪሎ ዋት ኃይል በማመንጨት 400 የሚሆኑ የዲንጋሞ ቀበሌ አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡ እንደ አስተባባሪው አሁን ላይ 97 በመቶ የፕሮጀክቱ ሥራ የተጠናቀቀ ሲሆን ቀሪው 3 በመቶ ከመብራት ገመድ ዝርጋታ ጋር የተያያዘ ነው፡፡
የካምባ ዙሪያ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ዓለሙ ጎንችሬ በሰጡት አስተያየት ፕሮጀክቱ ከዚህ በፊት ያልተሞከረና አካባቢያዊ ሀብትን በመጠቀም የልማት ጥያቄዎችን መፍታት እንደሚቻል ያመላከተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የወረዳው መንግሥት ፕሮጀክቱን ከማስተዳደርና በኃላፊነት ከመምራት ጋር ተያይዞ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጎን በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ቃል ገብተዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት