አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት መኖ ይዘትን እንዲሁም አዘገጃጀትን ለማሻሻል በእንስሳትና ዓሣ ሀብት ምርምር ማእከሉ ውጤታማ የምርምር ፕሮጀክቶችን እያከናወነ መሆኑ ተገልጿል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
በዩኒቨርሲቲው ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪት የሆኑት ዶ/ር አሸናፊ አዛገ እንደገለጹት ላለፉት 20 ዓመታት በእንስሳት ሳይንስ ዘርፍ በመምህርነትና በተመራማሪነት ያሳለፉ ሲሆን በዘርፉ እስከ 60 በመቶ የሚሆነውን ትልቅ ወጪ የሚይዘው መኖ ነው፡፡ በሀገራችን የመኖ እጥረት መኖሩንና ተደጋጋሚ ድርቅ የሚከሰት መሆኑን የጠቀሱት ተመራማሪው በትምህርት ላይ በነበሩባቸው ጊዜያት ያገኙት ተግባራዊ ልምምድ፣ ሀገራዊ ፍላጎቱ ትልቅ መሆኑ እና በትንሽ ወጪ በአካባቢ በሚገኙ ግብአቶች ውጤታማ ሥራ መሥራት የሚቻል መሆኑ ወደ ሥራው እንድገባ ገፋፍቶኛል ብለዋል፡፡
እንደ ተመራማሪው የወተት ላሞች ምርትና ዝርያ ማሻሻል ላይ ውጤታማ ለመሆን የተመጣጠነ መኖ እጅግ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በአካባቢው አርሶ አደሩ የበቆሎና ማሽላ አገዳን አድርቆ ለእንስሳት መኖነት የሚጠቀም ሲሆን ይህም የፕሮቲን ይዘቱ ሦስት በመቶ እንኳን የማይሞላ ነው ብለዋል፡፡ ምርቱ ሳይደርቅና አረንጓዴነቱ እንደተጠበቀ ሲለካ ከ9-11 በመቶ ፕሮቲን መገኘቱን ጥናታቸው እንዳሳየና በፕሮጀክቱ የበቆሎ ግንድና ቅጠልን ፈጭቶ በማብላላት የሚገኘውን ገፈራ/ Silage/ በማእከሉ ለሚገኙ ላሞች በመመገብ ለውጦችን ማግኘት መቻሉን ዶ/ር አሸናፊ ገልጸዋል፡፡
በፕሮጀክቱ መኖውን ለማዘጋጀት በቆሎን ከሌሎች የመኖ ዕፅዋት ጋር በማቀላቀል እየተሠራ ሲሆን በዝግጅት ሒደቱ በቆሎ በእሸትነት ደረጃ እያለ ተቆርጦ ፍሬው ለሰው ምግብነት ሲውል አገዳውና ቅጠሉን በመፍጨት በጉድጓድ ወይም በሌላ የተዘጋጀ ማቆያ ውስጥ አየር በማያስገባ ሁኔታ ተጠቅጥቆ ይሸፈናል፡፡ ከሦስት ቀናት በኋላ የማይጠቅሙና መኖውን የሚያበላሹ ኦክስጅን ፈላጊ ባክቴሪያዎች እየሞቱ ኦክስጅን የማይፈልጉ ላክቲክ አሲድ፣ አሴቲክ አሲድና ሌሎችም ጠቃሚ ባክቴሪያዎች እያደጉ ይሄዳሉ ያሉት ተመራማሪው ይህም ገፈራው የምግብ ይዘቱ ሳይቀንስና ሳይበላሽ እስከ አንድ ዓመት ድረስ ተጠብቆ እንዲቆይ እንደሚያደርገው ገልጸዋል፡፡ መኖው የመብላያ ጊዜውን ጨርሶ ለአገልግሎት ሲውል ነፋስ እንዳይገባ ከላይ ከላዩ እየተነሳ ወዲያው መሸፈን እንደሚገባ የተናገሩት ተመራማሪው በዚህ መልኩ የተዘጋጀው መኖ ለእንስሳቱ ሳቢ የሆነ መዓዛ ያለው፣ በቀላሉ አፋቸው ሳይጎዳ የሚበሉትና በቀላሉ የሚፈጭላቸው ሲሆን እንስሳቱ በወተትም ሆነ በሥጋ ተዋጽኦ ምርታማ እንዲሆኑ ያደርጋልም ብለዋል፡፡
ተመራማሪው በምርምር ማእከሉ ላሞች ላይ መኖ በመቀያየርና የተለያዩ ጥምረቶችን በመጠቀም የተደረገው የመጀመሪያ ዙር ሙከራ ትልቅ ለውጥ ማሳየቱን ገልጸው በቀጣይ አርሶ አደሩን በተለይም ሴቶችን በማሠልጠን የወተት ላም ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲሁም ወጣቶች ሥልጠና ወስደው በመደራጀት በዚሁ መንገድ መኖ ዝግጅት ላይ ወደ ሥራ እንዲገቡ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሮች ምርታቸውን በእሸት ጊዜ ሲቆርጡ፣ በዝናብ እጥረትና በሌሎችም ምክንያቶች ምርት በአረንጓዴነቱ ሲበላሽ እንዲሁም የተጠቀጠቀ እርሻን በሚያሳሱ /Tinning/ ጊዜ ገፈራ ማዘጋጀት እንደሚቻል የጠቀሱት ተመራማሪው ከበቆሎ በተጨማሪ ማሽላና ሌሎች ሰብሎችን እንዲሁም ለመኖነት የሚውሉ ሣሮች ቀላቅሎ በመጠቀም በዝናብ ወቅት በትርፍነት የሚገኘውን መኖ ጥራቱ ሳይቀንስ በማቆየት የመኖ ብክነትም ሆነ እጥረትን መከላከል ይችላሉ ብለዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እንስሳትና ዓሣ ሀብት ምርምር ማእከል ዳይሬክተር አቶ እሳቱ በቀለ ማእከሉ ከተቋቋመ ጥቂት ዓመታት ብቻ ያስቆጠረ ቢሆንም በወተት ላሞች፣ የሥጋና እንቁላል ጣይ ዶሮዎች፣ ዓሣ፣ ንብና ሌሎችም ላይ ዝርያ የማሻሻል እና ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የማድረግ ምርምሮችና ወደ መሬት የወረዱ ፕሮጀክቶችን መተግበሩን ተናግረዋል፡፡ የእንስሳት መኖ ማሻሻያ ፕሮጀክቱ ከሥራዎቹ አንዱ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ለሥራው ማእከሉ 1.75 ሚሊየን ብር መመደቡን ገልጸዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት