አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከትምህርት ሚኒስቴር እና ‹‹MasterCard Foundation››፣ ‹‹ASU›› እና ‹‹SYS›› ዓለም አቀፍ አጋር ተቋማት ጋር በመተባበር ‹‹e-SHE›› የተሰኘ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ትምህርት ማስጀመርና የተጠናከረ የትምህርት ሥርዓት መፍጠር የሚያስችል ፕሮጀክትን አስመልክቶ ጥቅምት 28/2017 ዓ/ም በሁሉም ካምፓስ ለሚገኙ መምህራን ኦሬንቴሽን ሰጥቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመማር ማስተማር በማካተት ዘመኑ የደረሰበት የእድገት ደረጃ መድረስ ይገባል ብለዋል፡፡ እንደ ሀገር በዲጂታል ቴክኖሎጂ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በሚደረገው ርብርብ መምህራን በቴክኖሎጂ የታገዘ ሳቢና ማራኪ የትምህርት አሰጣጥ ሂደት መከተል እንደሚገባቸው ፕሬዝደንቱ አሳስበዋል፡፡

የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ትግበራና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ሠረቀብርሃን ታከለ በበኩላቸው ሥልጠናው የከፍተኛ ትምርትን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ ውጤታማ የመማር ማስተማር ሂደት ለመፍጠር የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰው መምህራን ቴክኖሎጂውን በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ በማካተት ለትምህርት ጥራት የበኩላቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ 

የዩኒቨርሲቲው ‹‹e-SHE›› ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር መሐመድ አበበ እንደተናገሩት ዲጂታል ቴክኖሎጂውን ከትምህርት ሥርዓቱ ጋር በማጣመር አሁን ያለውን መማር ማስተማር የተሻለና ዘመኑን የዋጀ ማድረግ የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ ነው፡፡ በመሆኑም በዩኒቨርሲቲው ፕሮጀክቱን ለማስጀመር የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን መስጠት፣ በ‹‹e-SHE›› አተገባበር ላይ መረጃ የሚሰጥ ‹‹course.amu.edu›› የተሰኘ ድረ ገጽ መፍጠር፣ መሠረተ ልማቶችንና ግብኣቶችን ማሟላት፣ ለፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ ኮርሶችን መለየት እንዲሁም ‹‹e-SHE››ን ተቋማዊ የማድረግና ለውጤታማነቱ መምህራንና ተማሪዎች የሚኖራቸውን ድርሻ አስመልክቶ ሕገ ደንብ የማውጣት ሥራ ተሠርቷል፡፡ ዶ/ር መሐመድ አያይዘውም ለዲጂታል ቴክኖሎጂው አመቺ የትምህርት ይዘት ለማዘጋጀት፣ ዘርፉ የሚጠይቀውን ዕውቀት ለማዳበርና የመማር ማስተማሩን ሂደት ለማሻሻል ‹‹Master class›› የተሰኘ የ25 ሰዓት ሥልጠና ለመምህራን ይሰጣል፡፡ 

መምህራን በሰጡት አስተያየት ፕሮጀክቱ ለትምህርት ጥራት መሻሻል ቁልፍ ሚና ያለው በመሆኑ ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም የሚያስችል በቂ ግብኣት ማሟላትና ሥልጠናዎችን መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡

የአምስት ዓመት ፕሮጀክት የሆነው ‹‹e-SHE›› 50ዎቹ የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ሙሉ ለሙሉ አልያም በከፊል በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ መማር ማስተማር ሂደት ለማስጀመር የሚሠራ ሲሆን ግቡን ለማሳካት ‹‹MasterCard Foundation›› ድጋፍ በመስጠት፣ ‹‹SYS SHAYASHONG›› የማማከር ሥራ በመሥራት እንዲሁም በትምህርት ሚኒስቴር ዕውቅና ‹‹ASU›› የተሰኘ ዓለም አቀፍ የትምህርት ተቋም የምስክር ወረቀት በመስጠት በአጋርነት ይሠራሉ፡፡


አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት