የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሥራ ፈጠራ ልማት ማበልጸጊያ ማዕከል ከኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ከዩኒቨርሲቲው እና ከአርባ ምንጭ ፖሊ ቴክኒክና ሳታላይት ኢንስቲትዩት ለተወጣጡ መምህራን ከግንቦት 04-14/2016 ዓ/ም ተግባር ተኮር የኢንተርፕርነርሽፕ የአሠልጣኞች ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ሠልጣኞች ከሥልጠናው ያገኙትን ዕውቀትና ተሞክሮ እንደ አንድ የለውጥ ኃይል በመጠቀም በኢንተርፕርነርሽፕ ዘርፍ ለሀገሪቱ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ሊያበረክቱ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የሥራ ፈጠራ ልማት ማበልጸጊያ ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ወንድወሰን ጀረኔ እንደገለጹት ሥልጠናው በቀጣይ ጊዜያት ለተማሪዎች፣ ለወጣቶች እንዲሁም ለአርባ ምንጭ ከተማና አጎራባች የማኅበረሰብ ክፍሎች በኢንተርፕርነርሽፕና ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ሥልጠና ለመስጠት የሚያስችል የአሠልጣኞችን አቅምና ባሕርይ ማሻሻል ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ በሥልጠናው ብቁ የሆኑ አሠልጣኞች የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸው በመላ ሀገሪቱ የኢንተርፕርነርሽፕ አሠልጣኝና አማካሪ በመሆን የሚመደቡ ይሆናል፡፡
በኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት የኢንተርፕርነርሽፕ አሠልጣኝና አማካሪ ማስተር ፍሬው ዘውዴ ሠልጣኞች የልማት ኢንስቲትዩት የሥራ ባህሪያት የሆኑትን አምኖ መታመን፣ እርስ በእርስ መደጋገፍ እንዲሁም የዕውቀት ብቻ ሳይሆን የተግባር ሰው መሆንን በተሠማሩበት የሥራ መስክ ሊያሳዩ ይገባል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ማኅበረሰቡን ለማሠልጠን ከመሠማራታቸው በፊት ሥራቸውን መውደዳቸውን እንዲሁም ለማኅበረሰቡ ሕይወት የተሻለ ለውጥ ማምጣት መቻላቸውን መፈተሽና ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
በኢንስቲትዩቱ የአርባ ምንጭ ከተማ ሥራ ዕድል ፈጠራ አስተባባሪ ወ/ሪት ሙሉወርቅ በቀለ ዩኒቨርሲቲው መሰል ሥልጠናዎችን መስጠቱ ከአጋር ባለድርሻ አካላት ጋር ጠንካራ ትስስር እንዲኖረው ከማስቻሉም በተጨማሪ በኢንተርፕርነርሽፕ ዘርፍ የሚኖረውን የአሠልጣኞች እጥረት ችግር የሚፈታ ነው ብለዋል፡፡ ማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ ሥራ ከጀመረ ጀምሮ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ለተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከ76 ሚሊየን ብር በላይ የብድር አገልግሎት መስጠቱንና በተጨማሪም በንግዱ ዘርፍ ለተሠማሩ አካላት የገበያ ትስስር የመፍጠር ሥራዎች መሥራቱን አስተባባሪዋ ገልጸዋል፡፡
በአርባ ምንጭ ፖሊ ቴክኒክና ሳታላይት ኢንስቲትዩት የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ መምህርት ኢየሩሳሌም ሽጉጤ ሥልጠናው የተደበቀ ማንነቴን እንዳሳይ፣ በምሠራው ሥራ ጽናት እንዲኖረኝ እና በትክክለኛ የባህርይ ለውጥ ምንነት ላይ በቂ ዕውቀት እንዳገኝ አግዞኛል ብለዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት ት/ክፍል መምህር ዶ/ር አብዮት ጸጋዬ ሥልጠናው በሥራ ፈጠራ ምንነት ላይ ለማስተማር፣ በሥራ ፈጣሪነትና በንግዱ ዘርፍ የተሠማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ውጤታማ እንዲሆኑ እንዲሁም ከአካባቢያቸው ባሻገር ሀገር አቀፍ የቢዝነስ እይታ እንዲኖራቸው ፋይዳው የላቀ መሆኑን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት