የፌዴራል ጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ የልኡካን ቡድን በቅርቡ ተመርቆ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘውን የዩኒቨርሲቲው የማስተማሪያ እና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሺያላይዝድ ሆስፒታል አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ታኅሣሥ 5/2017 ዓ/ም ምልከታ እና ውይይት አካሂዷል፡፡ ጉብኝቱ በዋናነት የሆስፒታሉን እንቅስቃሴ በመገምገም መሻሻል ያለባቸውን ቦታዎች ለመለየት እና በሙሉ አቅም አገልግሎት እንዲሰጥ ትብብርን ለማጠናከርና ድጋፍ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
በጤና ሚኒስቴር የአገልግሎትና ፕሮግራም ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ ልዩ አማካሪ ፕ/ር ስለሺ ጋሩማ ጉብኝቱ የሆስፒታሉን ወቅታዊ አሠራርና አገልግሎት ዝርዝር ግምገማ ለማድረግ እና በቀጣይ ለሚደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍ አቅጣጫ ለመስጠት ያለመ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ፕ/ር ስለሺ የሆስፒታሉ ዘመናዊ የመሠረተ ልማት አውታሮች እና በጅማሬው የሥራ ምዕራፍ የተገኘው እድገት አመርቂ መሆኑን በማውሳት በቂ የሰው ኃይል፣ የገንዘብ እና ሌሎች ሊሟሉ የሚገቡ ጉዳዮች እንዳሉ ጠቁመዋል።
በሆስፒታሉ ዙሪያ በተለያየ ጊዜ በተደረጉ ውይይቶች በክልሉ የጤና አጠባበቅ አሰጣጥን ለማጎልበት በባለድርሻ አካላት መካከል ያለው ትብብር ወሳኝ ሚና እንዳለው ያወሱት ልዩ አማካሪው ሆስፒታሉ አስፈላጊ ሀብቶችን እንዲያገኝ ከበጀት ጋር የተያያዙ ተግዳሮቶችን መፍታት እና መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ንቁ ተሳትፎን ማጎልበት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። ሚኒስቴሩ በቅጥር፣ በሀብት ድልድል እና ቀጣይነት ባለው ክትትል አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑንም ልዩ አማካሪው አረጋግጠዋል።
በሚኒስቴሩ የሜዲካል አግልግሎት መሪ የሥራ ሂደት ውስጥ የሆስፒታል እና ዲያግኖስቲክ ዴስክ ኃላፊ አቶ ዐቢይ ዳዊት ልኡኩን በመወከል እንደተናገሩት የአምቡላንስ፣ የሕክምና ቁሳቁሶች እና በጤና አገልግሎት ድጋፍ ለማድረግ በትብብር መሥራት እንዲቻል በሆስፒታሉ ምልከታና ውይይት ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም በሜዲካል አገልግሎት መሪ የሥራ ሂደት ውስጥ በሚከናወኑ ዐበይት ተግባራት ዙሪያ፣ በጤና አገልግሎት ቴክኖሎጂ ሥርዓት፣ ሙያዊ ልየታና ሜዲካል ቱሪዝምን ለማስፋት ከባለድርሻ አካላት ጋር ጠንካራ ትብብር የመፍጠር ሂደት፣ የአደጋ እና ወሳኝ አገልግሎት፣ የሆስፒታልና ዲያግኖስቲክ ዴስክ ተግባርና ኃላፊነት፣ በኢትዮጵያ በሚገኙ ሆስፒታሎች መካካል ትብብርን በማጠናከር ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት እና ተደራሽነትን ለማስፋት መሥራት እንዲሁም የሕሙማን ልውውጥ ሥርዓትን ለማሳደግ አስቻይ ሁኔታዎች ላይ በባለሙያዎች ገለጻ እና ውይይት መደረጉን ገልጸዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል በአካባቢው ካሉ ሕሙማን ባሻገር ከአጎራባች አካባቢ የሚመጡትን በማስተናገድ የሆስፒታሉን አገልግሎት ለማስፋፋት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው ዩኒቨርሲቲው ከፌዴራል ጤና ሚኒስቴር እና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር አቅሙን ከፍ ለማድረግ እና የተቋቋመበትን ዓላማ በብቃት ለማሳካት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል፡፡
የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ደስታ ጋልቻ በሆስፒታሉ የእስከ አሁን ጉዞ አመርቂ ለውጥ መመዝገብ መቻሉን ገልጸው ይህን በማጠናከር ከሚፈለገው ደረጃ እና አቅም ለመድረስ ከተናጠል ተግባር ይልቅ የተቀናጀ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑን አስገንዝበዋል። በአገልግሎት ጥራት ላይ ቀጣይነት ያላቸው መሻሻሎችን ለማረጋገጥ ከዋና ዋና ባለድርሻ አካላት በተለይም ከፌዴራል ጤና ሚኒስቴር እና ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በትብብር ይሠራል ብለዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ የኮሌጁ የጤና ትምህርትና ሕክምና አገልግሎት ኮርፖሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ብርሃኑ አንዳርጌ የዩኒቪርሲቲውን አመሠራረት፣ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አጠቃላይ ሁኔታ እንዲሁም የሆስፒታሉ አሁናዊ ደረጃ፣ አገልግሎት አሰጣጥ፣ ተግዳሮቶች፣ መልካም አጋጣሚዎች እና እይታዎችን በተመለከተ ለልኡካን ቡድኑ በሰጡት ማብራሪያ መነሻነት ከተሳታፊዎች ጋር ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡
የልኡካን ቡድኑ በቀጣይ ከሆስፒታሉ አመራሮችና የሕክምና ባለሙያዎች ጋር በመገናኘት መረጃዎችን ለማሰባሰብ እና የተለዩትን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የተወያዩ ሲሆን የጤና ሚኒስቴር ሆስፒታሉ የአገልግሎት አቅሙን እንዲያጎለብት የበኩሉን ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብቷል፡፡ ጉብኝቱ እንደ ሀገር ከጤና አጠባበቅ ጋር ተያይዞ ያሉ የአቅርቦትና ሌሎች ጉዳዮችን ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተገልጿል።
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት