የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ እና ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ትኩረት የሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማዕከል ጋር በመተባበር በዝሆኔ ወይም የእግር እብጠት/Elephantiasis/ በሽታ ዙሪያ ከግንቦት 12-14/2016 ዓ/ም ከክልሉ ለተወጣጡ የጤና ባለሙያዎች በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ሥልጠናው በሽታው በብዛት ከሚከሰትባቸው ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ሲዳማ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ለተወጣጡ የጤና ባለሙያዎች በተከታታይ ሰባት ዙሮች እንደ ቦታው ቅርበት በክላስተር ተከፋፍሎ እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ትኩረት የሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ፕሮግራም ማኔጀር አቶ በላቸው ወክቾ እንደገለጹት በክልሉ ለዝሆኔ በሽታ የተጋለጡ በርካታ ሰዎች በመኖራቸው በሽታው ተባብሶ ለአካል ጉዳት ወይም ለሞት እንዳይዳርጋቸው ለመከላከል፣ ተላላፊ የሆነው ወደ ሌሎች እንዳይተላለፍ ለማድረግና የመረጃ ሥርዓቱን ለማጠናከር ለጤና ባለሙያዎቹ ሥልጠናው ተዘጋጅቷል፡፡ እንደ ማኔጀሩ ‹‹የተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች በሀገሪቱ ምን ያህል የጤና ችግር አስከተሉ?››፣ ‹‹ለመከላከል ምን መሥራት ይጠበቃል?››፣ ‹‹በሥራው ላይ ማን ማን መካተት አለበት?›› እንዲሁም ‹‹ከኅብረተሰቡ፣ ከመንግሥትና ከአጋር ድርጅቶች ምን ይጠበቃል?›› በሚሉ ጉዳዮች ላይ ሥልጠናው ግንዛቤ ያስጨብጣል፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ደስታ ጋልቻ ኢትዮጵያ በቆላማ አካባቢ በሽታዎች በከፍተኛ ደረጃ ተጠቂ ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን ጠቅሰው እስከ ሞት ከሚያደርሱ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች መካከል የሚጠቀሰውን ዝሆኔ በሽታ አስመልክቶ ለጤና ባለሙያዎች የሥራ ላይ ሥልጠና በመስጠት የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ የሥልጠናው ዓላማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ አካዳሚክ ዳይሬክተር ተወካይ ዶ/ር ዘርይሁን ዘርዶ በበኩላቸው ስለበሽታው ያለንን ዕውቀት በማጋራት ማኅበረሰቡ በበሽታው እንዳይጠቃ መከላከል፣ መረጃ መስጠት፣ መከታተልና እንክብካቤ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ትኩረት የሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች የምርምርና ሥልጠና ማዕከል ዳይሬክተር ረ/ፕ አብነት ገ/ሚካኤል በባዶ እግር ከመሄድ ጋር ተያይዞ አፈር ውስጥ ያለ ሲሊካ/Silica/ ንጥረ ነገር ወደ እግር ውስጥ በመግባት የፈሳሽ መዘዋወሪያ ቱቦዎችን በማጥበብና በመዝጋት እግር ውስጥ የፈሳሽ ክምችት እንዲኖር በማድረግ ለእግር እብጠት በሽታ እንደሚያጋልጡ ተናግረዋል፡፡ በሽታውን መከላከልና ማከም ብሎም በበሽታው የተያዙ ሰዎች ሕመሙ እንዳይባባስባቸውና ለከፍተኛ ጉዳት እንዳይጋለጡ የሥነ ልቦና ድጋፍ እንዲሁም በሽታው በሚገኝበት ጊዜ ምዝገባና ሪፖርት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡

የማዕከሉ ተመራማሪ ዓለማየሁ በቀለ በበኩላቸው ማዕከሉ ከተቋቋመ ጀምሮ በርካታ የምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን ማከናወኑንና ከጤና ሚኒስቴርና ከዓለም የጤና ድርጅቶች ጋር ተቀናጅቶ በርካታ ሥልጠናዎችን ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ ተላላፊ የሆነና ያልሆነ የዝሆኔ በሽታን አስመልክቶ ለ230 የጤና ባለሙያዎች ሥልጠና በመሰጠቱ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ የበሽታው መጠን እየቀነሰ መሆኑን ተመራማሪው ጠቁመዋል፡፡

የሥልጠናው ተሳታፊዎች በአስተያየታቸው በንድፈ ሃሳብና በተግባር ጠቃሚ ዕውቀት ማግኘታቸውን ተናግረው የቆላማ አካባቢ በሽታዎችም ሆነ ሕመምተኞች የተዘነጉ በመሆናቸው የማኅበረሰቡን አመለካከት በመቀየር በሽታዎቹን ለመግታት ከጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ጀምሮ በኃላፊነት ስሜት እንሠራለን ብለዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት