የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምርምርና ማኀበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አርባ ምንጭ ዲስትሪክት ጋር በመተባበር ከቅርንጫፉ ለተወጣጡ የኤሌክትሪክ ባለሙያዎች ከጥቅምት 21-23/2017 ዓ/ም የሙያ ብቃት ማሻሻያ ሥልጠና ሰጥቷል።ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
ሥልጠናው ‹‹Transmission line Models››፣ ‹‹Electric Safety››፣ ‹‹Synchronization›› እና ‹‹Load Balancing›› የሚሉ ዐበይት ርእሶች ተዳስሰውበታል፡፡
የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ ኢንስቲትዩቱ ከመማር ማስተማርና ምርምር ሥራዎች ባሻገር ሥልጠናዎችን በመስጠት በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለሙያዎች የተሰጠው ሥልጠናም የዚሁ ሥራ አካል ሲሆን ሥልጠናው በዋናነት ተግባርና ንድፈ ሃሳብን በማቀራረብ የተቋሙን አገልግሎት አሰጣጥ የሚያሻሽል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ኃላፊ ተወካይ አቶ ጌታነህ ተስፋዬ ተቋማቸው ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ ለመሥራት ባደረገው ስምምነት መሠረት ሥልጠናው መሰጠቱን ተናግረው ሥልጠናው በየጊዜው በባለሙያዎቻቸው ላይ የሚደርሱ አደጋዎችንና ችግሮችን የሚቀርፍ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በቀጣይ ጊዜያትም ከዩኒቨርሲቲው ጋር ተባብረን መሥራታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡
የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አዲሱ ሙሉጌታ ከዚህ ቀደም ባለሙያዎቹ መሰል ሥልጠናዎችን ለማግኘት አዲስ አበባ ድረስ ይሄዱ እንደነበር ተናግረው ከተቋሙ ጋር በተደረገ ውይይት ሥልጠናውን የመስጠት አቅም በዩኒቨርሲቲው በመኖሩ ሥልጠናው መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ አክለውም መሰል ሥልጠናዎች ማኅበረሰብን እና መንግሥትን የሚጠቅሙ በመሆናቸው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና ዕውቀትን በተለያዩ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ለሚሠሩ ባለሙያዎች ለማሸጋገር እንደ ኢንስቲትዩት በትኩረት ይሠራል ብለዋል፡፡
በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሲኒየር ተመራማሪና አሠልጣኝ ዶ/ር ያሊሾ ግርማ እንደገለጹት ሥልጠናው ባለሙያዎቹ በሥራ ወቅት የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች በመለየት የሙያ ክሂሎታቸውን ለማሳደግ እና ለማኅበረሰቡ የሚሰጡት ግልጋሎት ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ የተዘጋጀ ነው፡፡ ሥልጠናው በአራት ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ በማተኮር የተሰጠ ሲሆን የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም ላይ በቤተ ሙከራዎች ላይ ጭምር የተግባር ሥልጠና የተሰጠ መሆኑን ዶ/ር ያሊሾ አብራርተዋል፡፡
የሥልጠናው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ከሥልጠናው ለሥራ የሚውሉ መሣሪያዎች አጠቃቀም፣ ራስን ከአደጋ ለመጠበቅ በሚደረጉ ጥንቃቄዎች እና በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም ዙሪያ የተግባር ዕውቀት አግኝተናል ብለዋል፡፡ ሥልጠናው ከዚህ ቀደም ያሉብንን ክፍተቶች ያሳየን እንዲሁም ሥራዎችን ቴክኖሎጂን በመጠቀም የመሥራት ዕውቀትና ክሂሎት እንዳገኙም ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ ሥልጠናው ተጠናክሮና ሰፋ ያለ ጊዜ ተሰጥቶት ቢሰጥ የተሻለ እንደሚሆን አስተያየታቸውን ሰጥተው በሥልጠናው ባገኙት ዕውቀት ማኅበረሰቡንም ሆነ ተቋማቸውን በተሻለ ለማገልገል ቁርጠኛ መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት