የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሙያ ማበልጸጊያ ማዕከል ከ‹‹Dereja.com›› ጋር በመተባበር በ‹‹ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን›› አጋርነት ለቀጣሪ ድርጅቶች በቀጣሪዎች አቅም ግንባታ ፕሮግራም/Employers Capability Building/ ዙሪያ ነሐሴ 21/2016 ዓ/ም ገለጻ አድርጓል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ እንደገለጹት በተለያዩ ምክንያቶች በርካታ ወጣቶች ከምረቃ በኋላ በግልም ሆነ በቅጥር በቀላሉ ወደ ሥራው ዓለም አይቀላቀሉም፡፡ ያለው የሥራ ዕድል ውስን ከመሆኑ ባሻገር ቀጣሪዎች ተገቢውን መስፈርት የሚያሟሉ ተቀጣሪዎችን ለማግኘት ይቸገራሉ ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ ደረጃ ዶት ኮም ተቀጣሪዎችን ለማብቃት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱና ቀጣሪዎችን ለመደገፍ ይህንን መድረክ መፍጠሩ የሚደነቅና የሚያስመሰግነው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የሙያ ማበልጸጊያ ማዕከል አስተባባሪ መ/ርት ስለእናት ድሪባ የቀጣሪዎች አቅም ግንባታ ፕሮግራም ቀጣሪ ድርጅቶች በሚፈልጉት ልክ የሠለጠነ የሰው ኃይል እንዲያገኙ የሚያግዝና የሚደግፍ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ፕሮግራሙ በክልል ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተከናወነ የሚገኝና ወደ ሌሎች ክልሎች የመስፋፋት ዕድል ያለው መሆኑንም አስተባባሪዋ ጠቁመዋል፡፡

በቀጣሪዎች አቅም ግንባታ ፕሮግራም ዙሪያ ገለጻ ያደረጉት በአፍሪካ ጆብስ ኔትዎርክ የደረጃ ፕሮጀክት ማኔጀር አቶ አሸናፊ ብርሃኑ እንደገለጹት ደረጃ ዶት ኮም እ.ኤ.አ ከ2020 ጀምሮ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ‹‹Soft skill›› የሚባሉ ራስን ማወቅ፣ ራስን መግለጽ፣ የተግባቦት ክሂሎትና የሥራ ቃለ መጠይቅ ላይ ተመራቂ ተማሪዎችን በማሠልጠን ወደ ሥራ ዓለም እንዲገቡ ትኩረት አድርጎ ሲሠራ የቆየ ካምፓኒ ነው፡፡ ሠልጣኞቹን የሚቀበሉ ቀጣሪ ድርጅቶች ላይም መሥራት ተገቢ በመሆኑ የቀጣሪ ድርጅቶችን አቅም ለማሳደግ በሰው ኃይል አስተዳደር፣ ኢንተርንሽፕ እና የተመራቂ ተማሪዎች ምልመላ ላይ ግንዛቤ መስጠታቸውን አቶ አሸናፊ ተናግረዋል፡፡

የፕሮግራሙ ተሳታፊ የሆኑት የ‹‹S and D ሆቴሎችና ሪዞሪቶች›› ፕሮጀክት ማኔጀር አቶ ዮናስ አሰፋ እና የ‹‹አሸናፊ አርሼ የሕንጻ ሥራ ተቋራጭ›› ኮንስትራክሽን ማኔጀር አቶ ምንተስኖት አሸናፊ በሰጡት አስተያየት አዲስ የተመረቁ ተማሪዎችን ሲቀጥሩ የክሂሎት ክፍተቶችን እንዲሞሉ እንዲሁም ጽንሰ ሃሳብን ወደ ተግባር በአግባቡ እንዲቀይሩ ለማድረግ ግንዛቤ ያገኙበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት