የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ማኅበረሰተብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን ቸሀ ወረዳ በዘርፉ ለተሰማሩ ማኅበር አባላት በዘመናዊ የእንሰት መፋቂያ ማሽኖች አጠቃቀም ዙሪያ ከሰኔ 2-6/2017 ዓ.ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የማኅበረሰብ ጉድኝትና ኢንደስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ ዩኒቨርሲቲው ከባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር ላለፉት 6 ዓመታት በትብብር ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰው አሁን ላይ ትብብሩ አድጎ ለዚህ በመብቃቱ ለኢንስቲትዩቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በቅንጅት መሥራት ውጤታማ ለመሆን የሚረዳ በመሆኑ የቅንጅት ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ዶ/ር ቶሌራ ሠልጣኞች ከሥልጠናው የወሰዱትን ልምድ ወደ ተግባር በመለወጥ ውጤታማ ለመሆን እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡
የእንሰት ፕሮጀክት ዋና አስተባባሪ እና የባዮ ቴክኖሎጂ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ ሠልጣኞች ቴክኖሎጂውን መጠቀም ከመጀመራቸው በፊት በማሽኖቹ አጠቃቀም ላይ የተግባር ክሂሎት እንዲኖራቸው ታልሞ ሥልጠናው መሰናዳቱን ገልጸዋል። በተለያዩ ክልሎች ላይ ቴክኖሎጂውን ለማድረስ እየተሠራ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር አዲሱ ቴክኖሎጂዎቹ ለበርካታ ሥራ አጥ ዜጎች የሥራ ዕድል እየፈጠሩ መሆኑንም አስረድተዋል።
በባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የቴክኖለጂ ሽግግር ተመራማሪ ወ/ሮ አልማዝ ወርቁ ኢንስቲትዩቱ ከዩኒቨርሲቲው ጋር የእንሰት መፋቂያ ማሽኖችን በማፍለቅና ማዘመን ረገድ በጋራ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰው ቴክኖሎጂዎቹን ወደ ማኅበረሰቡ ተደራሽ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሥልጠናው ለሁለተኛ ዙር የተሰጠ መሆኑን የገለጹት ተመራማሪዋ የቀድሞ ሠልጣኞች ማሽኑን ተጠቅመው በመሥራት ሀብት ማፍራት መጀመራቸውን አስረድተዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ግምባሩ በላቸው በበኩላቸው ቴክኖሎጂው የእንሰት መፋቅ ሥራን ከነበረው ባህልዊ አሠራር ወደ ዘመናዊነት ያመጣ መሆኑን ገልጸው ማኅበረሰቡ እንሰት አብቃይና በስፋት ለምግብነት የሚያውል በመሆኑ በእጅጉ የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የማኅበሩ ሰብሳቢና ሠልጣኝ አቶ አዲሱ ንስቆ የዕድሉ ተጠቃሚ በመሆኑ ደስታ እንደተሰማው ገልጾ ማሽኑ ድካምን የሚያስቀር እና ጊዜና ጉልበትን የሚቆጥብ እንደሆነ ተናግሯል፡፡
የማኅበሩ ገንዘብ ያዥና ሠልጣኝ ወ/ሮ ይስሪሻ ሰክት ቴክኖሎጂው ቆጮን ከተለመደው አሠራር ውጪ በተለያየ መንገድ ለምግብነት ለማዋል እንደሚረዳ በተግባር ማየት እንደቻለች ገልጻ ይህም ለቀጣይ ሥራቸው አጋዥ እንደሆነ ተናግራለች።
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት