የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከኬር ኢትዮጵያ (Care Ethiopia) ዓለም አቀፍ ግብረ ሠናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ከጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ እና ቁጭሬ ወረዳ ለተወጣጡ 18 ወጣት ሴት አርሶ አደሮች በእንሰት መፋቂያ ማሽን አጠቃቀም ላይ ከጥቅምት 7-9/2017 ዓ.ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የኮሌጁ የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪ ዶ/ር ተስፋዬ ኃ/ሚካኤል በኮሌጁ ከመማር ማስተማር ባሻገር የማኅበረሰቡን ችግር ሊቀርፉ የሚችሉ በምርምር የተደገፉ ግኝቶችን በማቅረብ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ ላይ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የባዮቴክኖሎጂ ተመራማሪና የእንሰት ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ የእንሰት ቴክኖሎጂን ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለማስፋፋት ከተለያዩ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች ጋር እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከኬር ኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለመሥራት በተደረገ የመግባቢያ ስምምነት መሠረት ቴክኖሎጂዎቹን በሌሎች አካባቢዎች የማሳፋት አካል የሆነ የመጀመሪያ ዙር ሥልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ ጌዴኦ ዞን እንሰት አብቃይ በመሆኑ ቴክኖሎጂውን ማስተዋወቅና ማስፋት ጥራት ያለው ምግብ ወደ ገበያ እንዲገባ ከማስቻሉም በላይ እናቶች የተሻለ ምግብ እንዲያገኙ፣ ጊዜና ጉልበታቸውን በመቆጠብ የምግብ ብክነትን ለመቀነስ እንዲሁም የገቢያቸውን ለማሳደግ እንደሚያስችልም ዶ/ር አዲሱ አብራርተዋል፡፡ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ቴክኖሎጂውን ለማስፋት የተያዘው ዕቅድ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ተመራማሪው በመስኩ በጋራ ለመሥራት ለሚፈልጉ ተቋማት በዩኒቨርሲቲው በኩል ዝግጁነት መኖሩንም አረጋግጠዋል፡፡
በኬር ኢትዮጵያ የክትትልና ግምገማ ሲኒየር ማኔጀር አቶ ምንተስኖት ኢታና ፕሮጀክታቸው የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛን ማስቀረት ዋና ዓላማ አድርጎ እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡ በአብዛኛው ሕጻናት ለጉልበት ብዝበዛ የሚዳረጉት የወላጆች አቅም ማነስ ችግር በመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍ ጊዜና ጉልበት የሚቀንሱ ችግር ፈቺ የቴክኖለጂ ውጤቶችን በማቅረብ እና በሥልጠና በመደገፍ የሴቶችን የኢኮኖሚ አቅም በማጎልበት የኑሮ ደረጃቸውን ለማሻሻልና ሕጻንቱን ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲሄዱ ለማድረግ ታልሞ መሠራቱን አብራርተዋል፡፡ ሥራው ዘላቂና ውጤታማ እንዲሆን የብድር ተቋማት፣ ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ቢሮዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በጥምረት እየሠሩ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
የ‹‹RTN Ethiopia She Thrives Project›› አስተባባሪ አቶ ወንድሜነህ ግርማ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ከኬር ኢትዮጵያ ጋር በአጋርነት የሚሠራ መሆኑን ጠቅሰው በዋናነት ሴቶች ላይ የሚያተኩርና የሕጻናት የጉልበት ብዝበዛን ለማስቀረት የሚሰራ ነው ብለዋል፡፡ በሀገሪቱ መሰል ችግሮች የተዳረጉ በርካታ ሴቶች ያሉ በመሆኑ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ቴክኖሎጂውን በማስፋት ላይ ጠንክረው መሥራት እንዳለባቸውም አስተባባሪው ጠቁመዋል፡፡
ከጌዴኦ ዞን የመጡት ሠልጣኞች ወ/ሮ ፋንታነሽ መንግሥቱ እና ወ/ሮ ታደለች ደጀኔ በሰጡት አስተያየት የእንሰት ሥራ በእጅጉ አድካሚ፣ ከፍተኛ ጉልበትና ጊዜ የሚሻ መሆኑን ገልጸው በሥልጠናው በተግባር ያየናቸው አዳዲሶቹ ቴክኖሎጂዎች ከዚህ ቀደም የነበሩ ችግሮችን የሚቀርፉ ናቸው ብለዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት