በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሥራ ፈጠራና ሙያ ማበልጸጊያ ማዕከል እና በኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት (EDI) ትብብር ዓለም አቀፍ የኢንተርፕረነርሺፕ ሳምንትን በማስመልከት ጥቅምት 28/2018 ዓ/ም ለዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የኢንተርፕረነርሺፕ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የሥነ ትምህርትና ሥነ ባህርይ ሳይንስ ት/ቤት ዲን አቶ አንለይ ብርሃኑ ሀገራችን በየጊዜው እያደገች ከመሆኑ ጋር በተተያዘ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን በስፋት የሚፈልጉ የሥራ መስኮች መኖራቸውን ጠቅሰው የኢንተርፕረነርሺፕ ሥልጠናው ችግሮችን ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር ከራስ አልፎ ለሌሎች መፍትሔ ለማምጣት የሚያግዝ በመሆኑ በአግባቡ እንዲጠቀሙበት ለተማሪዎች መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
የዩኒቨርቲው የሥራ ፈጠራና ማበልጸጊያ ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር አብዮት ጸጋዬ ሥልጠናው ተማሪዎች ከሥራ ጠባቂነት ተላቀው የራሳቸውን ቢዝነስ መፍጠር እንዲችሉ ለማነቃቃት ያለመ እንዲሁም ተመርቀው ወደ ኢኮኖሚው ሲቀላቀሉ ሊገጥሟቸው የሚችሉ ፈተናዎችን በምን መልኩ ማለፍ እንደሚችሉ ግንዛቤ የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት (EDI) የአርባ ምንጭ ከተማ ፕሮጀክት አስተባባሪ ሙሉወርቅ በቀለ ተቋማቸው ከዩኒቨርሲቲው ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ላለፉት ሦስት ዓመታት የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዝደንት ጨምሮ ለአመራሮችና ለሴት መምህራን ሥልጠናዎችን መስጠታቸውን ያስታወሱት አስተባባሪዋ የአሁኑም ሥልጠና ቀደም ሲል በተቋማቸው በሠለጠኑ መምህራን የተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ አስተባባሪዋ ሥልጠናው ተማሪዎች በየአካባቢው ያሉ መልካም አጋጣሚዎችን በምን መልኩ ሊጠቀሙባቸው እንደሚችሉ የሚያሳይና የሥራ ፈጠራ አመለካከትን ለመጨመር የሚያግዝ ነው፡፡
የዩኒቨርሲቲው የማኔጅመንት ት/ክፍል መምህርና አሠልጣኝ ዐወል በከሪ እንደገለጹት የተማሪዎችን የቢዝነስ አመለካከት በመጨመር ከተቀጣሪነት ማውጣት፣ የራስን ካምፓኒ መፍጠር የሚያስችል የአእምሮ ቀረጻና ወደ ቢዝነስ መግባት የሚያስችል ተነሣሽነት(Business Opportunity Identification) መፍጠር ሥልጠናው ያተኮረባቸው ነጥቦች ናቸው፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት

