የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሥራ ፈጠራና ሙያ ማበልጸጊያ ማዕከል ከኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት (EDI) ጋር በመተባበር በፐብሊክ ኢንተርፕረነርሺፕ እና በኢንተርፕረነርሺፕ ቢዝነስ ማኔጅመንት ዙሪያ ለተከታታይ ቀናት ሲሰጥ የቆየው ሥልጠና ተጠናቋል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
ሥልጠናው ለ3 ተከታታይ ቀናት በፐብሊክ ኢንተርፕረነርሺፕ (PE) እንዲሁም ለ4 ተከታታይ ቀናት በኢንተርፕረነርሺፕ ቢዝነስ ማኔጅመንት ክህሎት (EBMS) ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 120 ለሚሆኑ የዩኒቨርሲቲው መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች መሰጠቱ ተገልጿል።
የዩኒቨርሲቲው የሥራ ፈጠራና የሙያ ማበልጸጊያ ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር አብዮት ፀጋዬ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ደረጃ ከፍ ለማድረግና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነቱን ለማሳደግ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ነድፎ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ሥልጠናውም የዚሁ የዓለም አቀፋዊነትና የተወዳዳሪነት ጉዞ አንድ አካል መሆኑን ጠቅሰው መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞችን በሥራ ፈጠራና ተቋማዊ ለውጥ ዙሪያ በማብቃት በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቁና ተወዳዳሪ የሆኑ፣ ችግሮችን የሚቀርፉና ተቋሙን ወደፊት ሊያሻግሩ የሚችሉ ባለሙያዎችን ለማፍራት ታስቦ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት የአርባ ምንጭ ቅርንጫፍ አስተባባሪ ወ/ሪት ሙሉወርቅ በቀለ በበኩላቸው ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ በአርባ ምንጭ ከተማ ሥራ ከጀመረበት ካለፉት 3 ዓመታት ወዲህ ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰዋል። በየዓመቱ የሚከበረውን «ዓለም አቀፍ የኢንተርፕረነርሺፕ ሳምንት» በማስመልከት በአርባ ምንጭ ለ3ኛ ጊዜ የተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተካሄዱ መሆኑን ጠቅሰዋል። አስተባባሪዋ አክለውም እስካሁን የዩኒቨርሲቲውን ከፍተኛ አመራሮች ጨምሮ ለተለያዩ የአመራር አካላት የኢንተርፕረነርሺፕ ሥልጠና ዎርክሾፕ (ETW) መሰጠቱንና በአሁኑ ወቅት 16 የሚሆኑ የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች የኢንስቲትዩቱ ቋሚ አባላት መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከግብርና ሳይንስ ኮሌጅ የመጡት ሠልጣኝ መምህር መሠረት ኡሩቆ፣ ሥልጠናው በውስጣቸው ያለውን እምቅ አቅም እንዲፈትሹ እንዳስቻላቸው ገልጸው፤ በመማር ማስተማሩ ሂደት የተከማቸ ዕውቀት በመሰል ሥልጠናዎች ሲታገዝ ወደ ገንዘብና ውጤታማ ሥራ ለመቀየር ትክክለኛ አቅጣጫ እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
በኢንተርፕረነርሺፕ ሥልጠና ዎርክሾፕ (ETW) ላይ እየተሰጠ ያለው ሥልጠና እስከ ኅዳር 16/2019 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን፣ ከኅዳር 17/2019 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ለተማሪዎች ተመሳሳይ ሥልጠና እንደሚጀመር ተገልጿል።
የመርሃ ግብሩ ማጠቃለያ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች እንዲሁም መምህራንና ተመራማሪዎች በተገኙበት ቅዳሜ ኅዳር 19/2019 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተመላክቷል።
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት

