በክረምት መርሃ ግብር በተለያዩ ኢንደስትሪዎች በሥራ ላይ ልምምድ የቆዩ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መምህራን ጥቅምት 05/2011 ዓ.ም የፋካልቲ ኃላፊዎች በተገኙበት የምልከታ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ
የዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ እንደገሉፁት ከዚህ ቀደም ይህንን የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም ለማስጀመር ጥረት ቢደረግም ሊሳካ እንዳልቻለ ገልፀው ፕሮግራሙ መምህራን በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ያላቸውን ዕውቀት በተግባር ልምምድ እንዲቀስሙ ከማስቻል ባሻገር ዩኒቨርሲቲው ከኢንደስትሪዎች ጋር ለሚፈጥረው ትስስር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርና መምህራን በቆይታቸው በኢንደስትሪዎች ውስጥ የሚታዩትን ችግሮች በመለየት የምርምር ሥራዎችን ለመስራት የሚያስችሉ ርዕሰ ጉዳዮችን እንዲያገኙ ከማድረግ አኳያ የሥራ ላይ ልምምዱ ሚናው የጎላ ነው ፡፡
የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር አቶ ጌታሁን ትዕግስቱ እንደገለፁት ከ2010 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ መምህራንን የተግባር ሥራ ክህሎት ክፍተት ለማሟላት መምህራኑን ወደ ኢንደስትሪዎች መላክ እንደተጀመረና ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ 9 መምህራን ወደ መከላከያ ኢንጂነርንግ ኮሌጅና ብረታ ብረትና ኢንጂነርንግ ኮርፖሬሽን መላካቸውንና የመምህራኑን ሪፖርት መሠረት በማድረግ መሟላት ያለባቸውን ክፍተቶች በመለየት በድጋሚ በሶስት ዙር መምህራኑን ወደ 3 የተለያዩ ኢንደስትሪዎች መላክ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ጌታሁን ማብራሪያ መምህራኑ በአንድ ወር ቆይታቸው ተማሪዎችን በሚያስተምሩት ጊዜ የተግባር ክህሎት ብቃት ለማዳበር የሚያስችሉ ግብዓቶችንና ለተግባር ምርምር ሥራ የሚያግዟቸውን ጽንሰ ሀሳቦች ላይ ግንዛቤ መጨበጣቸውን ከሪፖርታቸው መረዳት መቻሉን ተናግረው ወደ ፊትም ፕሮግራሙ በሰምስቴር መጨረሻና በክረምት ወራት ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
በመካኒካል ምህንድስና ፋካልቲ የቆዳ ኢንደስትሪ ኢንስቲትዩት ዕድገት አስተባባሪ እና ከሥራ ላይ ልምምዱ ተሳታፊዎች መካከል አንዱ የሆኑት ረ/ፕሮፌሰር ተሾመ ዳንጊሶ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከኢንደስትሪዎች ጋር ትስስር መፍጠሩ በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ የሚሰጠውን ትምህርት በተግባር አስደግፎ ለተማሪዎች ለመስጠት አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን ገልፀው መሰል የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራሞች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡