የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ከባህልና ቋንቋ ጥናት ተቋምና ከምርምር ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር ‹‹Female Presence in Research and Grant writing›› በሚል ርእስ ለዩኒቨርሲቲው ሴት መምህራን በምርምርና ግራንት አጻጻፍ ዙሪያ ከታኅሣሥ 01-04/2016 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ሥልጠናው የጥሩ ምርምር አሠራር፣ ምርምሮችን በተሻሉ ጆርናሎችና የምርምር መጽሔቶች ላይ ማሳተም፣ ለምርምር የሚያስፈልገውን ፈንድ ማፈላለግና የመሳሰሉ ክሂሎቶች ላይ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ተ/ፕ በኃይሉ ሴት መምህራን የተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ተቋቁመው የተሻሉ ምርምሮችን እንዲሠሩ፣ የትምህርት ደረጃቸውን እንዲያሳድጉ፣ ያሉባቸውን ችግሮች ተወያይተው መፍታት እንዲችሉ እንዲሁም ምርምሮችን በጋራ መሥራት የሚያስችላቸውን ሁኔታ እንዲያመቻቹ የሚያስችል ነውም ብለዋል፡፡

የምርምር ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም እ.ኤ.አ እስከ 2020 ድረስ በተደረገ ቆጠራ 78 የሚሆኑ ምርምሮች በሴቶች ተሳታፊነት የተሠሩ መሆናቸውንና በግራንድ ደረጃ በሴቶች የተሠራ ምርምር አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡ በዘንድሮው ዓመት አንድ ፕሮጀክት በሴቶች ተሳትፎ እየተሠራ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ተስፋዬ ይህም እንደ አጠቃለይ ከሴቶች ቁጥር አንጻር ሲታይ በጣም አናሳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዳይሬክተሩ ከዚህ ሥልጠና፣ ድጋፍና ተነሳሽነት አንጻር የሴቶች ተሳትፎ ከፍ ይላል ብለን እንጠብቃለን ብለዋል፡፡

ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሠናይት ሳህሌ ሥልጠናው ለሴት መምህራን በየዓመቱ የሚሰጥ መሆኑን አስታውሰው በዘንድሮው ዓመት 58 ሴት መምህራን በሥልጠናው መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደ ዳይሬክተሯ ከምርምር ዳይሬክቶሬት በተገኘው ወቅታዊ መረጃ መሠረት በዩኒቨርሲቲው ከሚያስተምሩ ሴት መምህራን መካከል 70 በመቶው በምርምር የሚሳተፉ ሲሆን መረጃው የሴት መምህራን የምርምር ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ያሳያል፡፡ የዋና ሴት ተመራማሪዎችን ቁጥር በተመለከተ ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና ከምርምር ዳይሬክቶሬት በኩል ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅ ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የባህልና ቋንቋ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ዶ/ር ሰኢድ አሕመድ በበኩላቸው በባህልና ቋንቋ ጥናት ተቋም 58 ምርምሮች የሚሠሩ መሆኑንና ከዚህም ውስጥ በስምንቱ ሴት ተመራማሪዎች የሚሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሥልጠናው በተቋሙ ያለውን አነስተኛ የሴት ተመራማሪዎች ቁጥር ታሳቢ አድርጎ የሚሰጥ መሆኑን ያወሱት ዳይሬክተሩ ከሥልጠናው በኋላ በሴት ተመራማሪዎች የጥናት ፕሮፖዛሎች ይመጣሉ ብለን እንጠብቃለን ብለዋል፡፡

ሥልጠናውን ከሳይንሱም ከልምዳቸውም እያጣቀሱ መስጠታቸውን የተናገሩት የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ፕሬዝደንትና በምሥራቅ አፍሪካ የሴት ተመራማሪዎች አነቃቂና አማካሪ ዶ/ር አልማዝ ባራኪ ሥልጠናው ሴት ተመራማሪዎችን ለምርምር ሥራ የሚያነቃቃ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከሠልጣኞቹ መካከል አምስት መምህራን (አንድ ከመቶ የሚሆኑት) 3 ዲግሪ ያላቸው መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር አልማዝ ይህም 3 ዲግሪ ያላቸው ሴት መምህራን ቁጥር አነሰተኛ መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡

ሌላኛው አሠልጣኝ የዩኒቨርሲቲው ኮምፒውቲንግና ሶፍትዌር ምኅንድስና ፋከልቲ መምህር አቶ አልዓዛር ባሕሩ ሥልጠናው ዲጂታል ዳታ ለመሰብሰብ ከሚረዱ የተለያዩ ሶፍትዌሮች አንዱ በሆነው ኦድኬ(odke) ሶፍትዌር ላይ ትኩረት አድርጎ መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡ ሶፍትዌሩ ዳታ ለመሰብሰብ የሚረዱ በወረቀት የተዘጋጁ መጠይቆችን ወደ ዲጂታል ለመቀየርና የተሰበሰቡትን መረጃዎች በማደራጀት ለምርምር ጆርናሎች ልኮ ለማሳተም የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ የገጠር ልማትና ግብርና ኤክስቴንሸን ት/ክፍል መምህርት ሠልጣኝ በረከቷ ደሌ ሥልጠናው መረጃ አሰባሰብና ምርምር አጻጻፍን አስመልክቶ ጥሩ ግንዛቤ ያገኙበትና ለምርምር ሥራ መነቃቃትን የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ጽሕፈት ክሂል በሥልጠናው ቢካተት መልካም መሆኑንም አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት