የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ለሴት መምህራንና ተመራማሪዎች ‹‹Grant Project Proposal Writing, Monitoring and Evaluation in line with Agenda 2030 and SDG Principles›› በሚል ርእስ ከሰኔ 5/2017 ዓ/ም ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ቀናት ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል በመክፈቻ ንግግራቸው ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ መሰል ሥልጠናዎች ከዩኒቨርሲቲው ዓላማዎች አንጻርም ሆነ ሴት መምህራንንና ተመራማሪዎች ለምርምር ሥራ ብቁ እንዲሆኑና ጥናቶቻቸውን ለኅትመት እንዲያበቁ ትልቅ ሚና አላቸው ብለዋል፡፡
የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደገለጹት በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ የትብብር ፕሮጀክቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ ሲሆን ቁጥሩ ካለው አቅምና ስፋት አንጻር ሲታይ አነስተኛ ነው፡፡ አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት ሴት ተመራማሪዎችና መምህራን በሥልጠናው ያገኙትን ዕውቀት ተጠቅመው በትብብር ፕሮጀክቶች ላይ ያላቸውን ተሳትፎና የአካዳሚክ ደረጃቸውን ከፍ ማድረግ እንዳለባቸው የተናገሩት ዶ/ር ተክሉ በጤና፣ ግብርና፣ ውኃና ሌሎችም መስኮች በሁሉም ካምፓሶች ላይ የሚገኙ ሴት ተመራማሪዎች በጋራ ተቀናጅተው እንዲሰሩ የመመሪያ ክለሳ እየተደረገ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ የእንስሳት ሳይንስ ት/ክፍል መምህርናና ተመራማሪ እንዲሁም አሠልጣኝ ፕ/ር ይስሐቅ ከቸሮ እንደገለጹት ሥልጠናው በግራንት ፕሮፖዛል አጻጻፍ ላይ በማተኮር የተሰጠ ሲሆን ይህም ሠልጣኞችን በተለያዩ ዓለም አቀፍ የፕሮጀክት ውድድሮች ላይ ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያግዛቸው ነው ብለዋል። እንደ ዩኒቨርሲቲ ብቁና ተወዳዳሪ በመሆን በቀጣይ ማኅበረሰቡንና ዩኒቨርሲቲውን የሚጠቀሙ ፕሮጀክቶችን ለማግኘት እንደሚረዳም ገልጸዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ከፍተኛ ባለሙያ ወ/ሮ ማርሸት ማቴዎስ እንደገለጹት ሥልጠናው ሴት ተመራማሪዎችና መምህራን በዓለም ዓቀፍ ፕሮጀክት ውድድር ላይ ተፎካካሪና አሸናፊ እንዲሆኑ ለማስቻል የተዘጋጀ ነው፡፡ ጽ/ቤቱ የሴቶችን አቅም ማጎልበት አንዱ ዓላማው በመሆኑ ሥልጠናው ማስፈለጉን የገለጹት ባለሙያዋ ዘመኑ የውድድር እንደመሆኑ ሴቶች ክሂሎታቸውን አሳድገው በራሳቸው የሚተማመኑና በዕውቀት ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ጽ/ቤቱ በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
የሥልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው ሥልጠናው ምርምርን በተመለከተ ለማንኛውም መምህርና ተመራማሪ እጅግ ጠቃሚ፣ በመስኩ ያለውን የክሂሎት ችግር የሚቀርፍ እና ለምርምር ሥራቸው አጋዥ መነሻ ሃሳቦችን የጨበጡበት መሆኑን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ሴት መምህራን በመቀናጀት በትብብር የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እንዲሠሩ ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊ ሁኔታዎችን ቢያመቻች ሲሉም ጠይቀዋል፡፡
በሥልጠናው መጨረሻ ለተሳታፊዎች የተሳትፎ ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት