የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ ሰብ ኮሌጅ የምርምር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ‹‹Improving the English Language Literacy Skills Performance of English Language Teachers through Flipped Phonics Training፡ The Case of Some Selected Primary Schools of Gamo Zone,Ethiopia›› በሚል ርእስ የአንደኛ ደረጃ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህራን የንባብና ጽሕፈት ችሎታ ማሻሻያ ላይ ጥናት ለማስጀመር ግንቦት 10/2016 ዓ/ም ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡ ጥናቱ በጋሞ ዞን ባሉ ምዕራብ ዓባያ፣ ጨንቻ፣ አርባ ምንጭ ዙሪያና ገረሴ ወረዳዎች እና ብርብርና ገረሴ ከተሞች ከ12-18 ትምህርት ቤቶችን የሚያካልል ሲሆን በአጠቃላይ 60 መምህራን ሥልጠናውን የሚያገኙ ይሆናል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሙሉጌታ ደበሌ እንደ ኮሌጅ ማኅበረሰብ ተኮር ምርምሮች በተጠናከረ መልኩ እየተሠሩ መሆኑን ገልጸው የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ይህ ፕሮጀክት እንዲሳካ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
በኮሌጁ የምርምር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር እንዳልካቸው ኃይሉ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በጽ/ቤቱ በኩል የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክሂሎትን ለማሻሻል ከሚሠሩ ፕሮጀክቶች አንዱና አመርቂ ውጤት ለማምጣት ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ላቲን ፊደልን በሚጠቀሙ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ፊደላቱ በእንግሊዝኛና በሌሎች ቋንቋዎች የሚያወጡት ድምጽ የተለያየ በመሆኑ ተማሪዎች ላይ ብዥታን የፈጠረ መሆኑን የሚናገሩት ኃላፊው መምህራኑን ማሠልጠኑ ተማሪዎችን ከጅምሩ ጥሩ መሠረት ለማስያዝ ይረዳል ብለዋል፡፡
የእንግሊዝኛ ቋንቋ ት/ክፍል መምህርና የፕሮጀክቱ ዋና ተማራማሪ ዶ/ር መለሰ መንገሻ ቀደም ሲል በተማሪዎች ላይ የተሠራ አንድ ጥናት በተማሪዎቹ ላይ ከፍተኛ የማንበብና የመጻፍ ችግር እንዳለ በማመላከቱ በዚህ መነሻነት ፕሮጀክቱ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ ችግሩን ለመፍታት መምህራኑን በማሠልጠንና በማብቃት ተማሪው ላይ ሠርተው ለውጥ እንዲያመጡ ማድረግ የፕሮጀክቱ ዓላማ መሆኑን ዶ/ር መለሰ ተናግረዋል፡፡ ችግሩ በመምህራኑ ላይም እንደሚታይ የገለጹት ተመራማሪው መምህራን በተለምዶ በክፍል ውስጥ የሚያስተምሩት በቂ ባለመሆኑ ፕሮጀክቱ የተለያዩ ተጨማሪ የማስተማሪያ ቪዲዮዎችን መምህራን በየቤታቸው ወስደው እንዲማሩ፣ ከአሠልጣኞቻቸው ጋር የተለያዩ ልምምዶችን እያደረጉ እንዲበቁ እና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ፊደላትና ድምጾችን ለይተው ማንበብና መጻፍ እንዲችሉ የሚያደርግ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ለጥናቱ 1.75 ሚሊየን ብር መመደቡንና በአራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ እንዲሁም ውጤቱ ታይቶ በቀጣይ ሥራው በስፋት እንደሚሠራ ተመራማሪው ጠቁመዋል፡፡
የጋሞ ዞን ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ ተወካይና የመምህራን የትምህርት አመራር ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሻራ ሻታ በመዝጊያ ንግግራቸው የፕሮጀክት ሥራውን በልዩ ትኩረትና ቅንጅት መሥራት እንደሚጠበቅ ጠቅሰው ፕሮጀክቱ ተማሪዎች ላይ የሚታየውን ብዥታ ለማጥራት ብሎም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡ እንግሊዝኛ ቋንቋ ሁሉንም ትምህርት ዓይነቶች ለመረዳት ወሳኝነት ያለው መሆኑን የገለጹት አቶ ሻራ ሥራውን በኃላፊነት በመወጣት ውጤታማ ማድረግና ለሌሎች ትምህርት ቤቶች ተደራሽነቱን ለማስፋት ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ችግሩ በተማሪና በመምህራን ዘንድ በስፋት የሚስተዋል መሆኑን ጠቁመው ወቅቱን ያማከለ ጥናት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ተሳታፊዎቹ ተማሪዎችን ለማሳወቅ መምህራን ትልቁን ድርሻ የሚይዙ በመሆኑ በታችኛው የትምህርት ክፍል ላይ በጋራ ለመሥራት መታቀዱ ለውጥ ለማምጣት እንደሚረዳ ተናግረው ለተግባራዊነቱ በሙሉ አቅም ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት