የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እና የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በጋሞ ዞን ጋጮ ባባ ወረዳ በደረሰው የመሬት መንሸራተትና የጎርፍ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሚውል ከ5 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው ሰብአዊ ድጋፍ አድርጓል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ዩኒቨርሲቲው ለተጎጂዎቹ  ካደረገው ድጋፍ መካከል  3,085,200 ብር ግምት ያላቸው 400 ሸሚዞች፣ 400 ቀሚሶች፣ 400 የሴት የውስጥ ልብሶች፣ 400 ሙሉ ኮቶችና ሱሪዎች እንዲሁም 400 ጥንድ የሴትና 400 ጥንድ የወንድ ጫማዎች ይገኙበታል። በተጨማሪም 600,000 ብር ግምት ያለው 100 ኩንታል ዱቄት በዩኒቨርሲቲው በኩል ለተጎጂዎቹ የቀረበ መሆኑ ተገልጿል።

ከዚህም ባሻገር ለዚሁ ሰብአዊ ተግባር ይውል ዘንድ ከዩኒቨርሲቲው መምህራንና አስተዳደር ሰራተኞች በአንድ ቀን ውስጥ 642,300 ብር፣ እንዲሁም ከተማሪዎች 700,000 ብር በድምሩ 1,342,300 ብር ጥሬ ገንዘብ ተሰብስቧል። በዚህ በተሰበሰበው ገንዘብም ለተጎጂዎቹ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ የምግብ ዘይት፣ ብርድ ልብስ፣ ጅባ፣ ወንበሮች፣ ብረት ድስቶች እና ፍራሾች ተገዝተው ድጋፍ ተደርገዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖች የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን በዩኒቨርሲቲው ስም በድጋሚ ገልጸው፣ ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ተመኝተዋል። ዩኒቨርሲቲውን ጥሪ ተቀበልው በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህንን ወገናዊ ድጋፍ ላደረጉ የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞችና ተማሪዎች በሙሉ ላቅ ያለ ምስጋናውቸውንም አቅርበዋል።

የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው እንደ ምርምር ተቋም ለመሰል የተፈጥሮ አደጋዎች ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት የሚያስችሉ የተቀናጀ ምርምሮችን ያደርጋል ብለዋል፡፡

የጋጮ ባባ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብሩክ ቡጻ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ አለኝታ የሆነ ተቋም መሆኑን ገለጸው በወረዳቸው የተለያዩ የማኅብረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የባባ ወንዝ ላይ ለተሰራው ድልድይ ግንባታ ከዲዛይን ጀምሮ በግንባታው ሂደት ወስጥ በርካታ ድጋፎችን ማድረጉን ያነሱት አስተዳዳሪው ዩኒቨርሲቲው በወረዳው ለደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ላደረገው ሰብአዊ ድጋፍ ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ


ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት