አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከኢፌዴሪ የቅርስ ጥናትና ምርምር ባለሥልጣን፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እና ከጋሞ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ጋር በመተባበር ‹‹ጋሞ ዱቡሻ ዎጋ››ን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስንና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ/UNESCO) በማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ በሚደረገው ሒደት ለተቋሙ የሚላኩ ሰነዶች ግምገማ እና ቀጣይ ሥራዎች ላይ የካቲት 4/2018 ዓ/ም በዩኒቨርሲቲው ወርክሾፕ ተካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደገለጹት ጋሞ ዱቡሻ ዎጋ ካለው ማኅበራዊ አበርክቶና የሰላም እሴት ማስጠበቅ አንጻር የቅርሱን ደኅንነትና ቀጣይነቱን ለማስጠበቅ ምዝገባው ከፍተኛ ፋይዳ አለው፡፡ በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው በጀትና የሰው ኃይል መድቦ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተለያዩ የጥናትና ምርምር፣ የድምጽና የምስል ስነዳ፣ የምዝገባ ሰነዶች ዝግጅትና ሌሎችም ሥራዎች ሲያከናውን ቆይቷል፡፡  

ምዝገባውን ለማከናወን ለዩኔስኮ የሚላኩ ሰነዶች በጥናትና ምርምር የተደገፉና ጥንቃቄ የሚሹ እንደመሆናቸው በተመራማሪዎቹ ተዘጋጅተው ለገምጋሚዎች መሰጠታቸውን የጠቀሱት ም/ፕሬዝደንቱ ከገምጋሚዎቹ የሚቀርቡ አስተያየቶችና የማስተካከያ ሃሳቦች ብሎም በመድረኩ የሚገኙ ግብዓቶችን በማካተት በቀጣይ የምርምር ማረጋገጫ ወርክሾፕ እንደሚዘጋጅ ጠቁመዋል፡፡ 

የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ ሁሉ በማከናወን የቅርሱን ምዝገባ እውን ለማድረግ ይሠራል ብለዋል፡፡ የውይይት መድረኩ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በባለቤትነት ስሜት ለሰነዱ መዳበርና ለምርምሩም ሆነ ለምዝገባው ስኬት የሚረዱ ሃሳቦችን ማቅረባቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

የምዝገባ ሰነዱን የዩኒቨርሲቲው የባህልና ቋንቋ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር መ/ር ታፈሰ ዋልኤ፣ የእንግሊዝኛ ቋንቋ እና ሥነ ጽሑፍ ት/ክፍል መምህር ዶ/ር ስንታየሁ ሰሙ እንዲሁም የኦስክፎርድ ዩኒቨርሲቲ የባህልና ሥነ ሰብ ተመራማሪና በተወለዱበት የጨንቻ አካባቢ ባህላዊ ሥርዓት የ‹‹ሁዱጋ›› መዓርግ የተሰጣቸው ዶ/ር ታደሰ ወልዴ የገመገሙት ሲሆን አስተያየቶቻቸውንም በወርክሾፑ አቅርበዋል፡፡ ገምጋሚዎቹ ሥነ ምድራዊ መግለጫዎች፣ የቋንቋ አጠቃቀም እንዲሁም የሚቀነሱ፣ የሚዳብሩና ማብራሪያ የሚሹ ሃሳቦች ላይ ምልከታዎቻቸውን በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን የወርክሾፑ ተሳታፊዎችም ለሰነዱ መዳበር የሚረዱ ሃሳቦችን አንሥተዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ዋና ተመራማሪ ዶ/ር ተመስገን ምንዋጋው ጋሞ ዱቡሻ ዎጋ ሰፊ የጥናት ጊዜ የሚፈልግና በውስን ገጾች ተገድቦ የማይገለጽ ሰፊ ቅርስ መሆኑን ጠቅሰው በዩኔስኮ መስፈርት መሠረት ሰነዱ የሚጠይቀው መረጃ በጥንቃቄና ገላጭ በሆነ መልኩ በማካከተት መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ ገምጋሚዎቹ በጥልቀትና በስፋት ሰነዱን ተመልከተው እጅግ ጠቃሚ ማስተካከያዎችንና ጥቆማዎችን ማቅረባቸውን ተመራማሪው ገልጸው አስፈላጊ ግብዓቶችን በማካተት ቅርሱ ተቀባይነት አግኝቶ ምዝገባው እንዲሳካ በልዩ ትኩረት እንሠራለን ብለዋል፡፡

በወርክሾፑ የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ዶ/ር ታደሰ ወልዴ፣ ከኢፌዴሪ ቅርስ ጥናትና ምርምር ባለሥልጣን አቶ ተስፋጽዮን ዮሴፍ እና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ዶ/ር ሰኢድ መሐመድ በበይነመረብ እንዲሁም ከክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ ከዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ፣ ከዞን አስተዳደር፣ ከዩኒቨርሲቲውና ከተለያዩ ተቋማት ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡


አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት