አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠበትን 13ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ከፌዴራል፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ ከልል እና ከጋሞ ዞን አስተዳደር የህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች ጋር በመተባበር ‹‹በኅብረት ችለናል›› በሚል መሪ ቃል የአባይ ዘመን ትውልድ የሥነ ጽሑፍ ምሽት ግንቦት 13/2016 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመሠረተ ድንጋይ ከተጣለበት ከመጋቢት 24/2003 ዓ/ም ጀምሮ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ከደመወዙ ሦስት ዙር ቦንድ እና ለህዳሴው ገቢ ለማሰበሳብ የተዘጋጀ ቶምቦላ በመግዛት፣ ተማሪዎች ከቀለባቸው በመቀነስ ሦስት ዙር ድጋፍ በማድረግ፣ የዩኒቨርሲቲው የውኃ ዘርፍ ምሁራን በግድቡ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት፣ በሚዲያ የግንዛቤ ማዳበሪያ ፕሮግራሞችን በማካሄድና ከውኃ ሀብት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ኮንፈረንሶችን እንዲሁም ከፌዴራል የህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ማስ/ጽ/ቤትና ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት ጋር የሥነ ጽሑፍ ምሽት ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የፌዴራል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ም/ኃላፊ አቶ ወርቁ ጓንጉል አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና የከተማው ነዋሪ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በቦንድ ግዥ እና በልገሳ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰው ዩኒቨርሲቲው ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በተለየ መልኩ በተከታታይ የሥነ ጽሑፍ ምሽቶችን ማዘጋጀት መቻሉ ተቋሙ ለህዳሴው ግድብ ግንባታ መሳካት የሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡ የሥነ ጽሑፍ ምሽቱ መርሃ ግብር የግድቡን ዓመታዊ በዓል ከማክበርና የሕዝቡን ግንዛቤ ከማሳደግ በተጨማሪ የክልሉንና የአካባቢውን ባህልና እሴት ለማሳደግ ሚናው የጎላ መሆኑንና በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አቶ ወርቁ ተናግረዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር አብደላ ከማል በሥነ ጽሑፍ ምሽቱ ‹‹Grand Ethiopian Renaissance Dam - The Pride of Ethiopians!›› በሚል ርዕስ የውይይት መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን ሀገራችን ኢትዮጵያ በርካታ የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር ውኃ እንዳላትና ከገጸ ምድር በዓመት 124 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውኃ እንዲሁም ከከርሰ ምድር ከ30-40 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ የሚገመት ውኃ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከውኃ ሀብቷ 10 በመቶ ብቻ ጥቅም ላይ ማዋሏንና በዘርፉ ሰፊ ሥራ እንደሚጠበቅ ብሎም በርካታ ተግዳሮቶችና ጫናዎች እንዳሉበት የገለጹት ዶ/ር አብደላ እነዚህን የውኃ ሀብቶች ዘመኑ በሚፈቅደውና ዓለም አቀፍ ሕግን በተከተለ መልኩ መጠቀም መቻል እንዳለብን አሳስበዋል፡፡ ዶ/ር አብደላ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ለሀገራችን ኢኮኖሚ መነቃቃት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል፡፡
በሥነ ጽሑፍ ምሽቱ በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የሚዘክሩ መነባነቦች፣ ግጥሞችና ዶክሜንተሪዎች የቀረቡ ሲሆን በተጋባዥ እንግዶች በዩኒቨርሲቲ አመራሮችና በታዳሚዎች የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርም ተካሂዷል፡፡ በመጨረሻም በመርሃ ግብሩ የተለያየ ሚና ለነበራቸው አካላትና የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን ላቀረቡ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት