አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ከአምስት መቶ ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ የደራሽ ምግብና የአምስት መቶ ሺህ ብር የጥሬ ገንዘብ ሰብአዊ ድጋፍ ሐምሌ 21/2016 ዓ/ም አድርጓል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
በዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዝደንት ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን የተመራው የልኡካን ቡድን በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውንና ሕይወታቸውን ያጡ ተጎጂዎች ቤተሰቦችን በስፍራው ተገኝተው አጽናንተዋል።
በአካባቢው በተፈጠረው የመሬት መንሸራተት አደጋ ሕይወታቸው ላለፉና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የተሰማቸውን ጥልቅና ልባዊ ሐዘን በራሳቸውና በዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ስም የገለጹት ም/ፕሬዝደንቷ ለሁሉም ቤተሰቦችና ለመላው የአካባቢው ነዋሪዎች መጽናናትን ተመኝተዋል። በቀጣይ ማኅበረሰቡን በዘላቂነት ለማቋቋም በሚደረግ ጥረት ውስጥ ዩኒቨርሲቲውና የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉም ወ/ሮ ታረኳ ገልጸዋል።
የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም በጎፋ ዞን ዛላና ኡባ ደብረ ፀሐይ በደረሱ የተፈጥሮ አደጋዎች ለተጎዱ ወገኖች በተመሳሳይ መልኩ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡ ዶ/ር ተክሉ ዩኒቨርሲቲው የምርምር ተቋም እንደመሆኑ የመሬት መንሸራተት አደጋ ወደ ደረሰበት ቦታ የተመራማሪዎች ቡድን በመላክ የአደጋውን መንስኤና በቀጣይ ዘለቄታዊ መፍትሔዎች ላይ ያተኮረ ጥናት እያካሄደ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ሳውላ ካምፓስ ኃላፊ አቶ ገብረመድኅን ጫሜኖ በበኩላቸው ይህ አስከፊ አደጋ በደረሰ ማግስት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት አደጋው በደረሰበት ስፍራ በመገኘት ተጎጂዎችን ማጽናናታቸውንና ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል መግባታቸውን አስታውሰዋል፡፡ በዚህም መሠረት ዩኒቨርሲቲው ላደረገው ድጋፍ እንደ አካባቢው ነዋሪና ተወላጅ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የጎፋ ዞን ም/አስተዳዳሪና የከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ ወሰኔ የተፈጠረው አደጋ ከሁለት መቶ በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች የሞቱበት እና መላው ኢትዮጵያውያንና ዓለምን ያሳዘነ አሰቃቂ አደጋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አደጋው ከተከሰተ ማግስት ጀምሮ የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዝደንት ጨምሮ በአካል በመገኘት ከሕዝባችን ጎን መሆናቸውን አሳይተዋል ያሉት አቶ ኤርሚያስ ዩኒቨርሲቲው ላሳየው አጋርነትና ተቋሙ ላደረገው የደራሽ ምግብና የገንዘብ ድጋፍ በዞኑ አስተዳደርና በሕዝቡ ስም ያላቸውን ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ አቶ ኤርሚያስ በተለይ ዩኒቨርሲቲው እንደ ምርምር ተቋም ለመሰል ችግሮች ዘላቂ መፍትሔዎች ማበጀት ላይ ምርምሮችን በማድረግ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የአስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዝደንት ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን፣ የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ፣ የሳውላ ካምፓስ ኃላፊ አቶ ገብረመድኅን ጫሜኖ እና ሌሎች የዩኒቨርሲቲው የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በአደጋው የተጎዱ ወገኖችን ለማጽናናት በስፍራው ከተገኙ መካካል ናቸው።
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት