በማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ ሰብ ኮሌጅ የጂኦግራፊና አካባቢ ጥናት ት/ክፍል ከጋሞ ዞን ከተማና ፕላን መምሪያ ጋር በመተባበር ከጥር 5-8/2017 ዓ/ም ለዞን፣ ለወረዳና ለከተማ አስተዳደር ስታትስቲክስ ባለሙያዎች በ‹‹GIS›› ምንነትና አጠቃቀም ላይ በኮሌጁ የGIS ማዕከል ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር አበራ ኡንቻ ት/ክፍሉ የመረጃ አያያዝን በቴክኖሎጂ የታገዘና ቀልጣፋ አሠራር የተከተለ ለማድረግ የባለሙያዎችን አቅም የሚያሻሽሉ ሥልጠናዎችን በመስጠት የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑንና ኮሌጁ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ በኮሌጁ የሚገኘውን የGIS ማዕከል ከክልል ባሻገር በሀገር አቀፍ ደረጃ የGIS ሥልጠና የልኅቀት ማዕከል ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ 

የጂኦግራፊና አካባቢ ጥናት ት/ክፍል ኃላፊ መ/ር አደፍርስ ተፈራ እንደገለጹት ሥልጠናው የስታትስቲክስ ባለሙያዎች በGIS የታገዘ ቀልጣፋና ተአማኒነት ያለው መረጃ የመሰብሰብ፣ የማደራጀትና የመተንተን እንዲሁም የተሻለ የውሳኔ አሰጣጥ ክሂሎት እንዲኖራቸው በቂ ግንዛቤ ማስጨበጥን ዓላማ ያደረገ ነው፡፡ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንዲሻሻል፣ የግብርና ምርትና ሥርጭትን አስመልክቶ ለሚመለከተው አካል መረጃ ለመስጠት፣ በቂ ጥናትና ምርምር ለማካሄድና ዕውቀትን ለማዳበር ሥልጠናው የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርሰሲቲው የ‹‹AMU-ESRI›› ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊና በጂኦግራፊና አካባቢ ጥናት ት/ክፍል መምህር ኃይለማርያም አጥናፉ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው አሜሪካ ከሚገኘው ‹‹ESRI›› የተሰኘ የGIS ሶፍትዌር አቅራቢ ድርጅት ጋር ስምምነት በመፍጠርና ነጻ ፈቃድ በማግኘት ላለፉት አራት ዓመታት በሶፍትዌሩ አጠቃቀም ላይ ለማኅበረሰቡ ሥልጠና ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ግንባር ቀደም የGIS ማሠልጠኛ ማዕከል ያለው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መሆኑን የጠቆሙት መ/ር ኃይለማርያም ከዩኒቨርሲቲው ጋር በትብብር በመሥራት ሥልጠናዎችን ወስደው ሙያዊ ክሂሎታቸውን ማዳበር ለሚሹ ተቋማትና ባለሙያዎች ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 

በጂኦግራፊና አካባቢ ጥናት ት/ክፍል ረ/ፕሮፌሰር ዓለሙ አሰሌ GPS በተለያየ መልክዓምድራዊ አቀማመጥ የሚገኙ መረጃዎችን በተገቢው መንገድ መሰብሰብ የሚያስችል ዘመኑ የደረሰበት የቴክኖሎጂ ውጤት መሆኑን ተናግረው በGPS የተሰበሰበውን መረጃ ወደ GIS ሶፍትዌር በመቀየር የተለያየ ውጤት ማግኘት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

በጋሞ ዞን ፕላንና ከተማ ልማት መምሪያ የስታትስቲክስና የGIS ቡድን መሪ አቶ ደግፌ ደምበላ በበኩላቸው የዞኑ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መረጃ አሰባሰብና አመዘጋገብ ስኬታማ እንዲሆን ሥልጠናው የላቀ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር የተሻለ ትብብር በመፍጠር የዞኑን ባለሙያዎች አቅም የሚያጎለብቱ ሥልጠናዎች እንደሚመቻቹም ተናግረዋል፡፡

በገረሴ ከተማ አስተዳደር የከተማው ፕላንና ልማት ቡድን መሪ አቶ ደሣለኝ ዳዊት በበኩሉ ሥልጠናው የከተማዋን የ10 ዓመት እቅድ በምናዘጋጅበት ወቅት እና የተሻለ የከተማ ካርታ ለማዘጋጀት የሚያግዝ መልካም አጋጣሚ መሆኑንና ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰቡን አቅም ለማሻሻል የሚያከናውናቸው ተግባራት የሚበረታቱ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ቅድመና ድህረ ምዘና፣ መሠረታዊ የGIS እና የGPS ምንነት፣ ሳይንሳዊ የመረጃ አሰባሰብ፣ አደረጃጀት እና አተናተን እንዲሁም የመሬት ይዞታ ካርታ አዘገጃጀት በሥልጠናው ከተዳሰሱ ርእሰ ጉዳዮች መካከል ናቸው፡፡ 

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት