በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሚገኙ የሜዲስንና ሚድዋይፈሪ የትምህርት ፕሮግራሞች ከኢፌዲሪ ትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን  Uገር አቀፍ አክሪዲቴሽን ማግኘታቸው ተገለጸ።ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የተሰጠውን ሀገር አቀፍ አክሪዲቴሽን አስመልክቶ ዛሬ ሰኔ 16/2017 ዓ/ም በተካሄደው መርሐ ግብር ላይ በ2017 ዓ/ም የኢፌዲሪ ትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን  እንደ ሀገር ለ5 ፕሮግራሞች ዕውቅና የሰጠ ሲሆን ከአምስቱ ሁለቱ ከላይ የተጠቀሱት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሮግራምች ናቸው።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር  አብደላ ከማል በሁለቱ ፕሮግራሞች የተገኘው ዕውቅና ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጸው ሌሎች የዩኒቨርሲቲው ኮሌጆችን የሚያነሳሳና አርአያ የሚሆን ነው ብለዋል። አንድ የትምህርት ፕሮግራም ጥራት አለው የሚባለው አክሪዲቴሽን ሲኖረው እንደሆነ የገለጹት ፕሬዝደንቱ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን እንዲሁም በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ተማሪዎች ጭምር መርጠው ወደ እኛ እንዲመጡ ለማድረግ ፕሮግራሞችን ዕውቅና እንዲኖራቸው ማድረግ ከፍተኛ የሆነ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡ በቀጣይ እንደ ዩኒቨርሲቲ በሌሎች ፕሮግራሞችም ዕውቅና ለማግኘት  የተጀመሩ ሥራዎች መጠናከር እንዳለባቸው የጠቆሙት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ዕውቅናው እንዲገኝ ለሰሩ የኮሌጁ አመራሮች ፣ መምህራንና የአስተዳዳር ሠራተኞች  ልባዊ ምስጋናቸውን በዩኒቨርሲቲው ስም አቅርበዋል።

የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር ቦጋለ ገብረ ማርያም በ2017 ዓ/ም በት/ሚኒስቴር እንድንፈጽም ከተሰጡን ቁልፍ ተግባራት (KPI) መካከል የትምህርት ፕሮግራሞችን አክሪዴት ማስደረግ ዋነኛው መሆኑን ገልጸው በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሚገኙ ሁለት ፕሮግራሞች ዕውቅና ማግኘታቸው እንደ ዩኒቨርሲቲ የሚያኮራን ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል። እንደ ሀገር የተቀመጡ ስታንዳርዶችን አሟልተው አክሪዲቴሽን ያላቸው ፕሮግራሞች ጥቂት መሆናቸውን የጠቀሱት ም/ፕሬዝደንቱ አክሪዲቴሽን የወቅቱ የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ በመሆኑ የተገኙ ልምዶችን በመጠቀም ሌሎች ፕሮግራሞች ዕውቅና እንዲያገኙ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ  ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ደስታ ጋልቻ ኮሌጁ በኢትዮጵያ ሚሊኒየም በ2000  ዓ/ም ሶስት የትምህርት ፕሮግራሞችን በመክፈት ሥራ የጀመረ ሲሆን አሁን ላይ በ27 የትምህርት ፕሮግራሞች ለሀገር አለኝታ የሚሆኑ ብቁ ዜጎችን በማፍራት ላይ ይገኛል ብለዋል። ኮሌጁ በተለያዩ ዘርፎች ስኬቶችን እያስመዘገበ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ደስታ በ 2017 ዓ/ም በተሰጠው ሀገራዊ የመውጫ ፈተና በስድስት ፕሮግራሞች ያስፈተናቸውን ተማሪዎች 100% ማሳለፍ መቻሉን ለአብነት ጠቅስዋል።

የፕሮግራም ዕውቅና የማግኘት ሂደቱ በርካታ ሂደቶችን ያለፈ እንዲሁም በርካታ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ከፍተኛ ጥረት የተደረገበት መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ደስታ በሁለቱ ፕሮግራሞች የተገኘው ዕውቅና እንደ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ እና በተማሪዎች ተመራጭ ተቋም ለመሆን ለሚደረገው ጥረት በር የሚከፍትና የራሱን ከፍተኛ ሚና የሚጫወት መሆኑን አስረድተዋል። እንደ ኮሌጅ ሌሎችን ፕሮግራሞች ሀገራዊ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ዕውቅና ለማስገኘች በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

በዕለቱ ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ አካባቢዎች በሽታዎች ሥልጠናና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ አብነት ገ/ሚካኤል  በኮሌጁ የበለጸገን በሥርዓተ-ትምህርቶች ውስጥ የተካተቱ ተግባራትና ስታንዳርዶች በአግባቡ መተግበራቸውን ለመቆጣጠር የሚያስችል "Curriculum Implementation Monitoring Dashboard" የተሰኘ ሶፍትዌርን አስመልክቶ ገለጻ ያቀረቡ ሲሆን የኮሌጁ የትምህርት ጥራት ዳይሬክተር አቶ አብነት ተሾመ በበኩላቸው በዕውቅና ማግኘት አጠቃላይ ሂደት፣ የገጠሙ ተግዳሮቶችንና ቀጣይ የዘርፉን የወደፊት ዕቅድን የተመለከተ ገለጻ አቅርበው ሰፊ ውይይት ተካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ማጠቃለያም ለሥራው ስኬት አስተዋጽኣ ላበረከቱ የአክ ሪዲቴሽን ኮሚቴ አባላት፣ የሥራ ኃላፊዎችና የሥራ ክፍሎች ዕውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት