የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት ለዩኒቨርሲቲው ክበባት ተጠሪ ተማሪዎች ጥር 20/2017 ዓ/ም በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከል ዙሪያ የሕይወት ክሂሎት የአሠልጣኞች ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ከአምላክነሽ ደሳለኝ ሥልጠናው በዩኒቨርሲቲው የተመደቡ ተማሪዎች በቆይታቸው የሕይወት ክሂሎታቸውን በማዳበር ራሳቸውንም ሆነ አቻ ጓደኞቻቸውን ለኤች.አይ.ቪ/ኤድስ አጋላጭ ከሆኑ ባሕርያትና ተግባር እንዲጠብቁና ጤናማ የትውልድ ተስፋ፣ መመኪያና ብቁ ዜጋ ሆነው መመረቅ እንዲችሉ የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ሠናይት ሳህሌ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች የሚገጥሟቸው ከሥነ ተዋልዶ ጤና ጋር የተያያዙ ችግሮችን በጥናት በመለየት ተጋላጭነታቸውን ለመቀነስ ለክበባት ተጠሪ ተማሪዎች ሥልጠናው መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ ሥልጠናው በዩኒቨርሲቲ ውስጥ በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ስርጭት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ አዎንታዊና አሉታዊ ሁኔታዎችን እንዲያውቁ፣ የአቻ ግፊትን መቋቋምና ስሜታቸውን መቆጣጠር እንዲችሉ የሚረዳ ነውም ብለዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የኅብረተሰብ ጤና ት/ክፍል መምህርትና የሥነ ተዋልዶ ጤና ባለሙያ አሠልጣኝ ፍሬሕይወት ኃይሌ እንደገለጹት የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ስርጭት ከዚህ ቀደም ቀንሶ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ በተደረገ ጥናት የተማሪዎች ተጋላጭነት እየጨመረ መምጣቱ ተመላክቷል፡፡ በመሆኑም ስርጭቱን ለመቀነስ እና ተማሪዎች ራሳቸውን ጠብቀው ዓላማቸውን አሳክተው ከዩኒቨርሲቲ እንዲወጡ ለማስቻል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎች ወሳኝ ናቸው፡፡
የሥልጠናው ተሳታፊ ተማሪ ሳሙኤል አባዋ በዩኒቨርሲቲ ቆይታችን ለኤች.አይ.ቪ/ኤድስ የሚያጋልጡንን ሁኔታዎች፣ ከዓላማ የሚያደናቅፉ መሰናክሎችና ልናደርግ ስለሚገባን ጥንቃቄ ከሥልጠናው ግንዛቤ አግኝተናል ብሏል፡፡ ተማሪዎች የመጡበት ዓላማ ላይ ብቻ በማተኮር እና የአቻ ግፊትን በመቋቋም ለስኬት ለመብቃት መሥራት እንደሚገባቸውም አስተያየት ሰጥቷል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት