የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያ እና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዛሬ ሐምሌ 9/2016 ዓ/ም በይፋ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ በአገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንትን ጨምሮ ሌሎች የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በመንግሥትና በዩኒቨርሲቲው ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ሲሠራበት የነበረው ግዙፍ ሆስፒታል የግንባታው ሥራ ተጠናቆና በግበዓት ተሟልቶ አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ ከፍ ያለ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል፡፡ ሆስፒታሉ በተወሰኑ የሕክምናና የምርመራ ክፍሎች ሥራ የጀመረ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ዳምጠው በሂደት በአካባቢው ባሉ ሌሎች የጤና ተቋማት በማይሰጡ የሕክምና አገልግሎቶች ላይ በማተኮር  በአራት ምዕራፎች የተከፈለ አገልግሎቶችን የማስፋት ዕቅድ ተዘጋጅቶ እየተሠራበት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የአስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዝደንት ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን ሆስፒታል ሕይወት የሚኖረው ለሕሙማን አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ብቻ መሆኑን ተናግረው በዛሬው ዕለትም ከከፍተኛ ትጋትና ልፋት በኋላ ይህ ሆኖ በማየታቸው ከፍተኛ ደስታ የተሰማቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለሆስፒታሉ ግንባታ ሥራ ከወጣው የላቀ ወጪ ሆስፒታሉን በግብዓት ለማሟላት ወጥቷል ያሉት ም/ፕሬዝደንቷ በቀጣይ እጀግ ከፍ ያሉና የተራቀቁ የልብ፣ የካንሰር፣ የፊዜዮቴራፒና ሌሎች በአካባቢው የሌሉ አገልግሎቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሥራ ለማስጀመር በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ በግብዓት በኩል ሆስፒታሉ አብዛኛው ነገር ተሟልቶለታል ያሉት ወ/ሮ ታሪኳ ከሰው ኃይል ቅጥርና ዝውውር አንጻር ያሉ እገዳዎች ተነስተው የሰው ኃይል ማሟላት እንዲቻል እየተሠራ መሆኑንም አክለዋል፡፡ ይህ ሲሆን የሆስፒታሉን አገልግሎት የመስጠት አቅም በእጅጉ ከፍ የሚያደርገው መሆኑንም ወ/ሮ ታሪኳ ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ደስታ ጋልቻ በበኩላቸው ሆስፒታሉ አገልግሎት እንዲጀምር ለማስቻል በልዩ ትኩረት ሲሠራ የቆየ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ሆስፒታሉ በተመላላሽ ሕክምና አገልግሎት እንዲጀምር ምቹ ሆኔታ መፈጠሩን አውስተዋል፡፡ እንደ አንድ የዩኒቨርሲቲው አመራርም ሆነ እንደ አካባቢው ነዋሪ በትልቅ ጉጉት ሲጠብቁት የነበረ መሆኑን የተናግሩት ዶ/ር ደስታ በሆስፒታሉ በውስን ዘርፎችች የተጀመረውን አገልግሎት ደረጃ በደረጃ ለማሳደግና ከፍ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሠራም አረጋግጠዋል፡፡

የጤና ትምህርትና ሕክምና አገልግሎት ኮርፖሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ብርሃኑ አንዳርጌ በበኩላቸው ሆስፒታሉ በሕጻናት፣ በማኅጸንና ጽንስ፣ በውስጥ ደዌና በቀዶ ጥገና ተመላላሽ ሕክምና እንዲሁም በተለያዩ የላቦራቶሪና የኤሜጂንግ ክፍሎች አገልግሎት የጀመረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሆስፒታሉ በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ከአንገት በላይ፣ የቆዳ፣ ከፍተኛ የሥነ አዕምሮና የዓይን ሕክምናን እንዲሁም የተኝቶ ሕክምና አገልግሎቶችን የተለያዩ የሁኔታ ግምገማዎች በማድረግ በሂደት የሚጀምር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሆስፒታሉ አገልግሎት ሲጠቀሙ ከነበሩ ተገልጋዮች መካከል አቶ አየለ ሣሙኤል የሆስፒታሉ ሥራ መጀመር ከፍተኛ ሕክምና ለማግኘት ሲባል ከዚህ ቀደም ማኅበረሰባችን ሲደርሰበት የነበረውን እንግልትና ከፍተኛ ወጪ የሚያስቀር በመሆኑ ከፍተኛ የሆነ የደስታ ስሜት እንደተሰማቸው ተናግረዋል፡፡ በሆስፒታሉ የተጀመረው አገልግሎት እንደ ጅምር በእጅጉ የሚበረታታ መሆኑን የተናገሩት አቶ አየለ በሂደት ሆስፒታሉ የአገልግሎት አድማሱን ለማስፋት ሊሠራ ይገባልም ብለዋል፡፡

በሆስፒታሉ ሥራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ የችግኝ ተከላ የተካሄደ ሲሆን ሥራ የጀመሩ የሥራ ክፍሎችም በዩኒቨርሲቲው አመራሮች ተጎብኝተዋል፡፡ በርከት ያሉ የአርባ ምንጭና አካባቢው ነዋሪዎች በሆስፒታሉ የሲቲ ስካንና ሌሎች አገልግሎት የጀመሩ ክፍሎች ሲገለገሉ ተስተውሏል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት