‹‹Huawei Technologies›› ኩባንያ በ ‹‹Huawei ICT Competition 2024/25›› ዙሪያ ለአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተማሪዎች ገለጻ ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
የ‹‹Huawei ICT Ecosystem Development›› ማኔጀር አቶ ታምሬ ዳውድ ‹‹Huawei›› በዓለም አቀፍ ደረጃ የቴሌኮም ዕቃዎችን በማምረት የሚታወቅ ኩባንያ ሲሆን ድርጅቱ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሁዋዌ አይሲቲ አካዳሚዎችን በመክፈት ለቴክኖሎጂ ተማሪዎች ነጻና ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ ሥልጠና እየሰጠ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ በአካዳሚው የሚሰጡ ሥልጠናዎች በተማሪዎችና በቀጣሪ ኢንደስትሪዎች መካከል ያለን ክፍተት በመሙላት ተማሪዎች ብቁና በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸው መሆኑን አውስተዋል፡፡ የዕለቱ መርሃ ግብርም የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ለ9ኛ ጊዜ በሚደረገው የ ‹‹Huawei ICT Competition 2024/2025›› ወድድር ላይ እንዲሳተፉና ብቁ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት የኔትወርክ አስተዳደር ቡደን መሪና የሁዋዌ አካዳሚ አስተባባሪ አቶ መኳንንት ኃይለሚካኤል የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከዚህ ቀደም በተደረጉ የሁዋዌ አይ ሲ ቲ ወድድሮች ላይ አመረቂና አኩሪ ውጤት ማስመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ በተደረገው የሁዋዌ አይሲቲ ውድድር ላይ በሁለት ዘርፎች 1ኛ በመወጣት ያሸነፉ ሲሆን በአህጉር ደረጃ ቱኒዚያ ላይ በተደረገ ውድድር 3ኛ ደረጃ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ቻይና ላይ በተደረገ ውድድር በተመሳሳይ 3ኛ ደረጃ በማግኘት አመርቂ ውጤት ማስመዝገባቸውን አውስተዋል፡፡ በመሰል ወድድሮች ላይ መሳተፍ እንዲሁም በአካዳሚው የሚሰጡ ሥልጠናዎችን መውሰድ የሥራ ዕድል ከማግኘት አንፃር ትልቅ ሚና ይኖረዋል ያሉት አቶ መኳንንት በዚሁ ሂደት ያለፉ 5 የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ትምህርታቸውን ሳይጨረሱ በሁዋዌ ኩባንያ መቀጠር ችለዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ከሁዋዌ የአይሲቲ ውድድር ባሻገር በዚሁ ድርጅት በሚዘጋጅ ‹‹Seeds for the Future program›› በተሰኘ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውድድር ላይ በመሳተፍ አበረታች ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ አቶ መኳንንት በውድድሩ ላይ መሳተፍም ሆነ አካዳሚውን በመቀላቀል የሚሰጡ ሥልጠናዎችን መውሰድ ያለውን ጠቀሜታ በመረዳት የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችም ሆነ መምህራን ምዝገባ በማድረግ አካዳሚውን እንዲቀላቀሉና የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ከገለጻው ተሳተፊዎች መካከል የሶፍት ዌር ምኅንድስና የ3ኛ ዓመት ተማሪ ክሩቤል ተስፋዬ የተሰጠው ገለጻም ሆነ ድርጅቱ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመሆን እየሰሩ የሚገኙት ሥራ ለተማሪዎች በእጅጉ ጠቃሚ መሆኑን ተናግሯል፡፡ በአካዳሚው የሚሰጠው ሥልጠናም ሆነ በውድድሩ የሚደረግ ተሳትፎ በሥራ ፍለጋ የምናጠፋውን ጊዜ በመቀነስ ረገድ እንዲሁም በውድድሩ ከተለያዩ ሀገራት የተወጣጡ ተማሪዎች የሚሳተፉ መሆናቸው በርካታ ልምዶችን እንድናገኝ ያግዘናል ብሏል፡፡
የሁዋዌ አይሲቲ ውድድር ጥራት ያለው የአይሲቲ ተሰጥኦ እድገትን ለማፋጠን፣ ለኢንደስትሪው ብቁ ተሰጥኦዎችን ለማዘጋጅትና ለመምረጥ እንዲሁም የመስኩ ባለተሰጥኦዎችን ወደፊት ለማቅረብ እየሰራ ይገኛል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት