የ2025 የጃፓን ወጣት የግብርና ተመራማሪዎች ዓለም አቀፍ ሽልማትን ላሸነፉት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት አቀባበልና የምሥጋና መርሐ ግብር ጥቅምት 21/2018 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል ዩኒቨርሲቲው በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ዕውቅና እንዲጨምር ማድረግና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ያለውን የትብብር ሥራዎች ማስፋት ተቋሙ በትኩረት ከሚሠራባቸው መስኮች መካከል ዋነኛው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በዚህ ረገድ ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ እየሠሯቸው የሚገኙ የትብብር ፕሮጀክቶችና ያገኙት ትልቅ ዓለም አቀፍ ሽልማት እንደ ተቋም እንድንኮራ ያደረገ ከመሆኑ ባሻገር ዩኒቨርሲቲውን በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስተዋወቅ የቻለ ትልቅ ስኬት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ 3 ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አንዱ የመሆን ራእይ ሰንቀናል ያሉት ፕሬዝደንቱ ይህን ራእይ ዕውን ለማድረግ እንደ ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ ያሉ ተቋምን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያስጠሩና ትብብሮችን የሚፈጥሩ ተመራማሪዎች በብዛት ያስፈልጉናል ብለዋል፡፡ ዶ/ር አዲሱ እስከ ዛሬ ላስመዘገቡት ስኬትና እንደ ተቋም ላስገኟቸው ዕውቅናዎች ያላቸውን አድናቆትና ልባዊ ምስጋና ያቀረቡት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ተመራማሪው በቀጣይ ለሚሠሯቸው ሥራዎች ዩኒቨርሲቲው እንደሁልጊዜውም አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ከጎናቸው እንደሚሆን አረጋግጠዋል፡፡

የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በጃፓን የተገኘው ዓለም አቀፍ ዕውቅናና ሽልማት እንደ ዩኒቨርሲቲ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር የሚያኮራ ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል። ዶ/ር አዲሱ ከዩኒቨርሲቲ አልፈው ሀገርን ጭምር ማስጠራታቸው በእጅጉ የሚያስደስትና የሚያስመሰግናቸው መሆኑንም ዶ/ር ተክሉ ተናግረዋል፡፡ የጃፓኑ መድረክ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ስም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ያለበት ነበር ያሉት ዶ/ር ተክሉ ጃፓን ከሚገኙ የተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብር ለመሥራት የሚያስችሉ ንግግሮችና ግንኙነቶች የተደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ አጋጣሚው ጃፓን ከሚገኙ እንደ ጃፓይጎ ካሉ ትልልቅ ተቋማት ጋር በትብብር እንድንሠራ አጋጣሚ የፈጠረ መሆኑንና ግንኙነቶችን አጠናክሮ መጠቀም እንደሚገባ ዶ/ር ተክሉ በንግግራቸው አንስተዋል፡፡ የዶ/ር አዲሱ ሥራ ለሌሎች የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተመራማሪዎች ትልቅ አርአያ የሚሆን እንደሆነም ም/ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡

የአስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዝደንት ፕ/ር ጳውሎስ ታደሰ በበኩላቸው ዶ/ር አዲሱ በስኬታማ ሥራቸው እንደ ተቋም ከምናደንቃቸውና ከምንሳሳላቸው ምሁራን መካከል ናቸው ብለዋል፡፡ ዶ/ር አዲሱ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ከሀገር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅ እያደረጉ የሚገኙ ምሁር መሆናቸውን የገለጹት ም/ፕሬዝደንቱ ከምንም በላይ ተቋምን በማስቀደም እየሠሩ ላሉት ድንቅ ሥራ ያላቸውን አድናቆትና አክብሮት ገልጸዋል፡፡

የምርምር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያም ዶ/ር አዲሱ በየጊዜው አዳዲስ ሃሳቦችን በማፍለቅ በተሳተፉበት የፈጠራና ምርምር ሥራዎች ውድድር ሁሉ አሸናፊ የሚሆኑ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲ እንደ ዶ/ር አዲሱ ያሉ ተመራማሪዎች በስፋት ያስፈልጉናል ያሉት ዶ/ር ተስፋዬ ሌሎች የዩኒቨርሲቲያችን መምህራንና ተመራማሪዎች ተሞክሮ በመውሰድ ከሀገር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ መፍጠር የሚችሉ ሥራዎችን ለመሥራት  እንዲተጉ መክረዋል፡፡

ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ ያገኙትን ሽልማት ተከትሎ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ላደረጉላቸው ደማቅ አቀባበልና በተሰጣቸው አክብሮት ልባዊ ደስታ የተሰማቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ያገኙት ዓለም አቀፍ ሽልማት ለቀጣይ ሥራ በእጅጉ የሚያነሳሳቸው መሆኑን የገለጹት ዶ/ር አዲሱ ለዚህ ስኬት እንዲበቁ አብረዋቸው ሲሠሩ የነበሩ የሥራ ባልደረቦች፣ በየደረጃው ያሉ የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና መላው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኀበረሰብ ድጋፍ ትልቅ ሚና እንደነበረው ገልጸዋል፡፡ አሁን ላሉበት የስኬት ደረጃ ለመድረስ በርካታ ውጣ ውረዶችን ማለፋቸውን የገለጹት ዶ/ር አዲሱ ልምድና ተሞክሯቸውን ለሌሎች የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተመራማሪዎች ለማካፈል ዝግጁ መሆናቸውንም አውስተዋል፡፡

የመርሐ ግብሩ ተሳታፊዎች ዶ/ር አዲሱ ከግል ጥቅም ይልቅ የተቋምን ጥቅም የሚያስቀድሙ፣ በትብብርና በቡድን ሥራ የሚያምኑ፣ በየጊዜው አዳዲስ ሃሳቦችን በማፍለቅ ተግባራዊ የሚያደርጉ ምሁር መሆናቸውን በመግለጽ ለተመራማሪው ያላቸውን አድናቆትና አክብሮት ገልጸዋል፡፡ 

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ 19ኛውን የጃፓን ዓለም አቀፍ ወጣት የግብርና ተመራማሪዎች ሽልማት በማሸነፍ የተቋሙን ስም በማስጠራታቸው ያዘጋጀውን የዕውቅና የምሥክር ወረቀት አበርክቷል፡፡

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት