በአዲሱ የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች መዋቅራዊ አደረጃጀት ለውጥ መሠረት በዩኒቨርሲቲው እየተካሄደ የሚገኘው የሠራተኞች ድልድል በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የተላከውን የአፈጻጸም መመሪያ እንዲሁም ሌሎች በተለያየ ጊዜ የተላኩ አጋዥ መመሪያዎችን መሠረት አድርጎ የተፈጸመ መሆኑን የድልደላ ኮሚቴው ገልጿል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የሠራተኞች ድልድል ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አየልኝ ጎታ የደልዳይ ኮሚቴው መመሪያው በሚፈቅደው መሠረት ተደራጅቶ የራሱን የትግበራ ዕቅድ በማዘጋጀት ነሐሴ 2015 ዓ/ም ሥራ መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡
እንደ አቶ አየልኝ በአዲሱ የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች መዋቅራዊ አደረጃጀት ለውጥ መሠረት በፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በተላከው የአፈጻጸም መመሪያ ዙሪያ በሁሉም ካምፓሶች ለሚገኙ አጠቃላይ ሠራተኞች ግንዛቤ የተፈጠረ ሲሆን በሂደትም ለዩኒቨርሲቲው ተፈቅደው የመጡ የሥራ መደቦችን በማሳወቅ ሠራተኛው በየካምፓሱ በተዘጋጀ የውድድር ቅጽ ምርጫውን እንዲሞላ ተደርጓል፡፡
አቶ አየልኝ በውድድሩ ከአምስት ሺህ በላይ ሠራተኞች የተሳተፉ ሲሆን የእያንዳንዱን ሠራተኛ የውድድር ምርጫ እንዲሁም አግባብነት ያለው የትምህርት ዝግጅትና የሥራ ልምድ በአግባቡ ማጣራትና የእያንዳንዱን ሠራተኛ ፕሮፋይል ማዘጋጀት ሰፊ ጊዜ ወስዷል ብለዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ኮሚቴው የሠራተኞች የትምህርት ዝግጅት ትክክለኛ የአሠራር ሥርዓትን ተከትሎ የተገኘ መሆኑን በስፋት ሲያጣራ የቆየ ሲሆን በዚህም የ76 ሠራተኞች የትምህርት ማስረጃ ሥርዓትን ተከትሎ የተገኘ አለመሆኑ እንዲሁም የ4 ሠራተኞች የትምህርት ማስረጃ ሙሉ በሙሉ ፎርጅድ መሆኑ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡
ከቡድን መሪ በላይ ባሉ የኃላፊነት መደቦች ላይ ሲካሄድ የቆየው የድልድል ሥራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ በድልድሉ ውጤት መሠረት የምድባ ደብዳቤ ተሰጥቶአቸዉ ሠራተኞች ሥራ ጀምረዋል ያሉት አቶ አየልኝ
ይህም ሥራ በከፍተኛ ጥንቃቄ መመሪያና ደንብን ተከትሎ የተፈጸመ መሆኑን አውስተዋል፡፡ በኃላፊነት መደቦች ላይ የሚወዳደሩ ሠራተኞች የብቃት መለኪያ ፈተና እንዲወስዱ መመሪያው የሚያዝ በመሆኑ የፈተናውን ፍትሐዊነትና ሚዛናዊነት ለማረጋገጥ ፈተናው ሙሉ በሙሉ በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ተዘጋጅቶ እንዲሰጥና ውጤቱም እንዲገለጽ ተደርጓል፡፡ ከዚህም ባሻገር በመመሪያው መሠረት በኃላፊነት መደቦች ላይ በሚደረገው ውድድር ላይ በዩኒቨርሲቲው የበላይ ኃላፊ ከሠላሳ ከመቶ የሚሞላ የአመራርነት ብቃት ምዘና አንዱ ሲሆን ይህም ሥራ ተወዳዳሪዎች ለዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ባቀረቡት ስትራቴጂክ ዕቅድና በተደረገላቸው ቃለ መጠይቅ መሠረት ተመዝነው ውጤቱ መሞላቱን ሰብሳቢው አውስተዋል፡፡
ከቡድን መሪ በታች ያሉ መደቦች ላይ የተደረገው የድልድል ሥራ ተጠናቆ ውጤቱን ለሠራተኞች ይፋ አድርገናል ያሉት አቶ አየልኝ በመመሪያው መሠረት በውጤቱ ላይ ቅሬታ ያላቸው ሠራተኞች ቅሬታቸውን ለቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አቅርበው እየታየላቸው ይገኛል፡፡ አሁን ላይ የድልድል ኮሚቴው አብዛኛውን ሥራ ጨርሷል ያሉት አቶ አየልኝ ከዚህ በኋላ ቀሪ ሥራ የሚሆነው የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ የቅሬታ ምላሽ ሲሆን ምላሹን ተከትሎ በድጋሚ የሚታዩ ጉዳዮች ካሉ ደልዳይ ኮሚቴ የሚያይና የሚያስተካክል ይሆናል፡፡ በዚህ አግባብ ሥራው ሲጠናቀቅ ለሠራተኞች የምደባ ደብዳቤ ተዘጋጅቶ እንደሚሰጣቸው አቶ አየልኝ ገልጸዋል፡፡ አቶ አየልኝ በዚህ ሂደት ለዩኒቨርሲቲው የማስተማሪያ እና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሚሆኑ አዳዲስ የሥራ መደቦች ተፈቅደው መምጣታቸው ሠራተኛውን በእጅጉ የጠቀመ መልካም አጋጣሚ ሲሆን ምደባ ሳያገኙ ተንሳፈው የነበሩ ሠራተኞች መደብ እንዲያገኙ በከፍተኛ ሁኔታ ረድቷልም ብለዋል፡፡
የድልድል ሂደቱ መመሪያዎችን ተከትሎ በተጠያቂነትና በኃላፊነት ስሜት የተመራና የተፈጸመ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት አቶ አየልኝ ነገር ግን አንዳንድ ግለሰቦች በማኅበራዊ ሚዲያ ጭምር ድልድሉን አስመልክተው የሚያሰራጩት መረጃ ከእውነት የራቀና ትክክለኛ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከሚቴው በአጠቃላይ የድልድል ሥራውን አስመልክቶ ቅሬታ ውይም ጥያቄ ያለውን አካል ለማስተናገድና ተገቢውን መረጃ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ያረጋገጡት አቶ አየልኝ በአጠቃላይ የሥራው ሂደት እዚህ ደረጃ እንዲደርስ በትጋት የበኩላቸውን ለተወጡ የደልዳይ ኮሚቴ አባላት፣ የካምፓስ የሰው ሀብት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ለዩኒቨርሲቲው አመራሮች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የድልድል ከሚቴው አባልና የሠራተኞች ተወካይ የሆኑት ወ/ሮ ስንታየሁ እጅጉ በበኩላቸው ከሥራው ውስብስብነትና አንጻር ላለፈው አንድ ዓመት ያህል ኮሚቴው ሙሉ ጊዜውን ሰጥቶ ሲሠራ ቆይቷል ብለዋል፡፡ በርካታ ሠራተኞች የትምህርት ዝግጅታቸውንና የሥራ ልምዳቸውን ባላገናዘበ መልኩ ከፍ ባሉ መደቦች ላይ ለመወዳደር ቅጽ የሞሉ መሆኑና የተወዳደሩበትን ሁለት መደቦች ማጣታቸው እንደ ኮሚቴም ሆነ እንደ ሠራተኛ ተወካይ በእጅጉ የተቸገሩበት ጉዳይ እንደነበር ወ/ሮ ስንታየሁ ተናግረዋል፡፡ እነዚህን ምንም መደብ ያላገኙ ሠራተኞች በአፈጻጸም መመሪያው መሠረት ክፍት በቀሩ መደቦች ላይ በኮሚቴ እንዲመደቡ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ የምደባና ድልደላ ሂደቱ በግልጽነትና የድልድል አፈጻጸም መመሪያውን ተከትሎ የተፈጸመ መሆኑን የኮሚቴ አባሏ አስረድተዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት