አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከምክትል ፕሬዝደንቶች፣ ከኢንስቲትዩቶች፣ ከኮሌጆች፣ ከተለያዩ የሥራ ክፍሎችና ከምርምር ማዕከላት ጋር የ2018 ዓ/ም ቁልፍ ተግባራት አፈጻጸም ውል (KPI) ጥቅምት 18/2018 ዓ/ም ፊርማ ሥነ ሥርዓት አካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል በበጀት ዓመቱ የተሰጡ ቁልፍ ተግባራትን በአግባቡ መፈጸምና አመርቂ ውጤት ማስመዘግብ ከሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ የሚጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኮሌጆች ተቆጥሮ የተሰጧቸውን ተግባራት ለትምህርት ክፍሎች፣ ትምህርት ክፍሎችም ተግባራቱን ከግለሰብ መምህራን ጋር በመፈራረም መሥራት እንደሚገባ በአጽንኦት የተናገሩት ፕሬዝደንቱ ዩኒቨርሲቲው በየጊዜው ቁልፍ ተግባራቱን መሠረት አድርገው ሥራዎች እየተከወኑ መሆኑን በትኩረት እንደሚከታተል ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከስምንቱ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ውድድር ውስጥ መሆኑንና በዚህም በየጊዜው ግምገማና ምዘና እንደሚደረግ የገለጹት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ቁልፍ ተግባራቱን እንደ ተቋም ያለን አቅም አሟጦ በመጠቀምና ተደጋግፎ በመሥራት መፈጸም የህልውና ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በ2018 የትምህርት ዘመን በርከት ያሉ ተማሪዎች ተመድበዋል ያሉት ፕሬዝደንቱ ያሉንን ተማሪዎች በአግባቡ መያዝ፣ ተገቢውን አገልግሎት በጥሩ ሁኔታ መስጠት፣ በአግባቡ በማስተማር ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የማድረግ ጉዳይ ከምን ጊዜውም በላይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ በንግግራቸው አንስተዋል፡፡ ተማሪዎች ላይ የምንሠራው ሥራና የምንፈጥራቸው ምቹ ሁኔታዎች በቀጣይ ዩኒቨርሲቲያችን በተማሪዎች ዘንድ ይበልጥ ተመራጭ እንዲሆን የሚረዳ በመሆኑ ኮሌጆች በዘርፉ ላይ ተግተው እንዲሠሩ አበክረው አሳስበዋል፡፡

በቅርቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በወጣ የዩኒቨርሲቲዎች ደረጃ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች 7ኛ ደረጃን ያገኘ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝደንቱ ጠንክረን ከሠራን ከ1-3ኛ ደረጃን መያዝ የማንችልበት ምንም ምክንያት የለም ብለዋል፡፡ ለዚህም ከምንጊዜውም በላይ ያሉን መልካም ዕድሎች አሟጦ መጠቀም እንዲሁም በትብብር፣ በቁርጠኝነትና በአንድነት መሥራት የግድ እንደሚል አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡


ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት