የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ጥር 14/2015 ዓ/ም በኩልፎና አባያ ካምፓሶች በሚገኙ የቤተ ሙከራ ክፍሎች ምልከታ በማድረግ በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲ ምርምሮች የሚሠሩበትን ሂደት በማመቻቸት፣ በማደራጀትና በማዘመን ጥራት ያለው የምርምር ውጤት እንዲወጣ መሥራት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡ በቤተ ሙከራዎቹ አበረታች ተግባራትን መመልከታቸውን የጠቀሱት ተ/ፕሬዝደንቱ ምልከታው እንደሚቀጥል እና ቤተ ሙከራዎችን በግብአት ለማሟላት በልዩ ትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡
የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው ቤተ ሙከራዎችን በአግባቡ ማደራጀትና በግብአት ማሟላት ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ገልጸው ቀደም ብለው በግዥ የመጡ ንብረቶች ወደ ሥራ የማስገባት ሥራ እንደሚሠራ አመላክተዋል፡፡ አክለውም ሳይንስ በየጊዜው የሚሻሻል በመሆኑ አዳዲስና ወቅታዊ የቤተ ሙከራ መሣሪያዎችን ማሟላት እንደሚገባ እና የቤተ ሙከራ ቁሳቁስ ያልተሟሉበት ላይ ቅድሚያ በመስጠት እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በርካታ የቤተ ሙከራ ግብአቶች በተቋሙ መኖራቸውን ገልጸው ሁሉም የተቋሙ የቤተ ሙከራ ተጠቃሚ መገልገል የሚችልበት ማዕከላዊ ቤተ-ሙከራ በዩኒቨርሲቲው መቋቋም እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ ለቤተ ሙከራ የሚመጡ ተጨማሪ ግብአቶችን ተጠቅሞ በጋራና በኃላፊነት ለለውጥ ጠንክሮ በመሥራት የተቋሙን ዕቅድ ማሳካትና ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ቀዳሚና ትኩረት የሚሰጠው ተግባር ሊሆን እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት