የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ህግ ትምህርት ቤት «አስዴፖ» (ASDEPO) ከተሰኘው ሀገር በቀል ድርጅት ጋር በመተባበር በሚሰራው ፕሮጀክት ከኮንሶ ዞን ካራት ዙሪያ ወረዳ ለተወጣጡ የፍትህ አስፈጻሚዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሱ ወንጀሎችና ተያያዥ ጥቃቶችን መከላከል ላይ ያተኮረ ስልጠና ጥቅምት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ሰጥቷል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በስልጠና መድረኩ ላይ የኮንሶ ዞን ካራት ዙሪያ ወረዳ አስተዳደር ተወካዮች፣ የፍርድ ቤት ፕሬዝደንቶች፣ ዳኞች፣ የፍትህ ጽሕፈት ቤት ባለሙያዎችና ኃላፊዎች፣ ዓቃቢያነ ህግ፣ የሴቶችና ህጻናት፣ የፖሊስ፣ ከጤና ተቋማት የተወከሉና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ታድመዋል።

የህግ ትምህርት ቤት ዲን አቶ አብርሃም ክንፈ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው ከ«አስዴፖ» ሀገር በቀል ድርጅት ጋር በመተባበር በዞኑ ለአቅመ-ደካሞች ነፃ የህግ ድጋፍ መስጫ መዕከላትን በማቋቋም በትምህርት ቤቱ በኩል ነጻ የሕግ አገልግሎት እየተሰጠ ነው፡፡ ከድርጅቱ ጋር በጋራ ከሚሰራው ስራ አሁን የተሰጠው ስልጠና ሁለተኛ ዙር መሆኑን የጠቀሱት ዲኑ፣ የፍትህ ሰጪ ባለድርሻ አካላት በየዕለት ተዕለት የስራ እንቅስቃሴያቸው ማወቅና መተግበር የሚገባቸውን መሬት ላይ ያለውን ሀቅ ከህግ አንፃር ማስገንዘብ እንዲሁም ወደፊት መሥራት የሚገባቸውን የትኩረት ቦታዎች ለመለየት የዕለቱ መርሃ ግብር ዓላማ መሆኑን አስረድተዋል።

አቶ አብርሃም እንደገለጹት፤ ጥቃት የደረሰባት ሴት ከአካላዊ ጉዳቱ በተጨማሪ በፍትህ እጦት ምክንያት ለተደጋጋሚ የስነ-ልቦና ስቃይ ትዳረጋለች። ይህም ከፍትህ አካላትና ባለድርሻ አካላት ቸልተኝነት፣ ወንጀለኛውን የሚያበረታቱ አሰራሮች እና በማህበረሰቡ ውስጥ ከሚታዩ ጎጂ የባህል እይታዎች የሚመነጭ ነው፤ በመሆኑም ይህ መርሃ ግብር በጥቃት ተጋላጮች ላይ የሚደርሰውን ህመም ለማከምና አስፈላጊውን እንክብካቤ በቅንጅት ለማቅረብ ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።

በስልጠናው ወቅት የህግ ትምህርት ቤቱ መምህራን በተለያዩ አርዕስተ-ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ የሥልጠና ጽሁፎችን አቅርበዋል። መምህር ደረጄ ማሞ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት በኢትዮጵያ ህግ አንፃር ያለውን እይታ ያቀረቡ ሲሆን፣ መምህር ራህማቶ ሰርጋጋ በበኩላቸው ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች በኢትዮጵያ የወንጀልና ተያያዥ ህጎች የሚሰጣቸውን ምላሽ ተንትነዋል። አሰልጣኞቹ እንደገለጹት፤ ችግሩን ያለባለሙያዎች ንቁ ጥረት መቅረፍ የማይቻል በመሆኑ፣ ስልጠናው የህግ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ጉዳዩን በጥልቀት እንዲረዱና በወቅታዊ መረጃዎች ተደግፈው ጥቃቱን ለመከላከል የሚያስችል አቅም እንዲፈጥሩ የሚያስችል ነው፡፡

በሌላ በኩል መምህር እምሻው ተሾመ የሴቶች ሰብአዊ መብቶች እና በባህላዊ የግጭት አፈታት ሂደት ያላቸውን ሚና አስመልከተው  ገለጻ ሰጥተዋል፡፡ በተጨማሪም የባህላዊ የግጭት መፍቻ መንገዶች ምንነት፣ ከመደበኛው የፍትህ ስርዓት ያላቸው መለያ ባህሪያት፣ ለማህበረሰቡ ያላቸው ጥቅም እና በባህላዊ የግጭት አፈታት ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ ምን እንደሚመስል አብራርተዋል።

 

መምህር እምሻው አክለውም፣ የሴቶች ተሳትፎ በውሳኔ ሰጪነት ላይ አናሳ ቢሆንም ተሳትፏቸው ተቀባይነት ያለው ውሳኔና አዲስ እይታ በማምጣት ግጭትን በዘላቂነት ለመቅረፍና ሰላምን ለማረጋገጥ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል። ህገ-መንግስቱ ባህላዊ የግጭት መፍቻ መንገዶችን የሚደግፍ በመሆኑ፣ ይህንን መብት ተጠቅሞ ሴቶችን በዘመናዊውም ሆነ በባህላዊው አሰራር በማሳተፍ የሚደርስባቸውን ጥቃት መከላከል፣ የተሻለ የሴቶች ጥበቃ እንዲኖር ማድረግ እና በማህበረሰቡ ባህል ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ እንዲጎላ አስገንዝበዋል፡፡

የስልጠናው ተሳታፊዎች አቶ አዲስዓለም ገረሙ፣ አቶ እንግዳ ዳዋንቶ እና አቶ ዘነበ ሰንበቶ በሰጡት አስተያየት፤ የስልጠናው የቀረበው ሰነድ ሙያዊ ቅርርብ ለሌላቸውም ጭምር ጥሩ ግንዛቤ ያስጨበጠ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዘርፉ እንደ መንግስት የተሰራበት ቢሆንም ነባራዊ ለውጥ በአካባቢው የማይታይ መሆኑን ጠቁመዋል። በመሆኑም ተከታታይነት ያለው ስልጠና እስከ ታችኛው እርከን በመወረድ ሊሰጥና ዘርፉ በጥናት ተጠናክሮ በትኩረት ሊሰራበት እንዲሁም ለውጥ ለማምጣት የጋራ ትግልና ጥረት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

በመጨረሻም ከሰልጣኞች ጥያቄና አስተያየት የቀረበ ሲሆን፣ ከመድረኩ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

 ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

 የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት