የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ት/ቤት በጋሞ ዞን ቦረዳ ወረዳ ለሚገኙ የወረዳና ማኅበራዊ ፍርድ ቤት ዳኞች፣ የሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ጽ/ቤት፣ ወንጀል መርማሪ ፖሊሶች፣ የመሬት ዴስክና ከሌሎች ሴክተር መሥሪያ ቤቶች የተወጣጡ ባለሙያዎች በአዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመሬት ዴስክ አዋጅ፣ በሴቶች ጥቃትና ጾታዊ ትንኮሳ እንዲሁም የማኅበራዊ ፍርድ ቤቶች ሥልጣንና ተግባር ዙሪያ ጥቅምት 1/2017 ዓ.ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የቦረዳ ወረዳ ፍርድ ቤቶች አስተዳደር አቶ እንድርያስ ጩቃሎ ዩኒቨርሲቲው በወረዳው ለሚገኙ የተለያዩ ባለሙያዎች የሰጠው ሥልጠና ለማኅበረሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት የሚያሻሽል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ሠልጣኞች ከሥልጠናው የሚያገኙትን ዕውቀት በመጠቀም ማኅበረሰቡን በተሻለ መንገድ ለማገልግል እንዲዘጋጁም ኃላፊው መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት ዲን ተወካይና የትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ ጉድኝት ጽ/ቤት አስተባባሪ አቶ ጌትነት ደባልቄ የሕግ ት/ቤት አቅመ ደካማ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ ለሴቶች፣ ለአረጋውያንና ለአካል ጉዳተኞች ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት በመስጠት ማኅበረሰቡን በሰፊው እያገለገለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ረገድ ዩኒቨርሲቲው 14 የሕግ ድጋፍ ማዕከላት ያሉት መሆኑን የጠቆሙት አቶ ጌትነት ከዚህም ባሻገር ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ መንገዶች የፍትሕ አካላትን አቅም የሚገነቡ ሥልጠናዎችን ሲሰጥ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ በቦረዳ ወረዳ የተሰጠው ሥልጠናም የዚሁ ሥራ አካል መሆኑን ኃላፊው አብራርተዋል፡፡

የሕግ ት/ቤት መ/ር ብላቴ ብሳሬ በአዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የገጠር መሬት አዋጅ ዙሪያ ሥልጠና የሰጡ ሲሆን አዋጁ ከቀድሞው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል መሬት አዋጅ ጋር ሲነጻጻር ብዙ አዳዲስ ነገሮችን ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሥልጠናው ሠልጣኞች አዋጁ ላይ ተመሥርተው ሥራቸውን እንዲሠሩ በማድረግ አዋጁን በሚገባ ካለመገንዘብ የሚመጡ ችግሮችን ያስቀራልም ብለዋል፡፡
የሕግ ት/ቤት መምህርት የሆኑት ሀገርወርቅ ደሳለኝ በበኩላቸው ‹‹ወሲባዊና ጾታዊ ትንኮሳን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች›› በሚል ርእስ ሥልጠና የሰጡ ሲሆን በዚህም ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሕጎችንና ድንጋጌዎችን በመጥቀስ ርእሰ ጉዳዩን በጥልቀት ለማስገንዘብ መሞከራቸውን ገልጸዋል፡፡ ዓላማውም በሴቶች ላይ በሚደርሱ ጾታዊና ወሲባዊ ትንኮሳዎች ዙሪያ ባሉ ድንጋጌዎች ላይ ግንዛቤ ማስጨበጥ መሆኑን አውስተዋል፡፡

የቦረዳ ወረዳ ሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አማረች አይዛ ከሥልጠናው በኋላ በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው በተለይ በሴቶች ዘርፍ ላይ ለሚሠሩ ባለሙዎች በዘርፉ አቅም የሚፈጥር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት