የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት ከኮርያ መንግስት የልማት ኤጀንሲ (KOICA) በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ፣ አስዴፖ (ASDEPO) ከተባለ ሀገር በቀል ድርጅት እና ከተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) ጋር በመተባበር በሰገን ዙሪያ ወረዳ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ጥቅምት 28 ቀን 2019 ዓ.ም በጉማይዴ ከተማ ሰጥቷል። ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
ስልጠናው በቤተሰብና በንብረት ህግ መሰረታዊ ደንቦች፣ የኢ-መደበኛና ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓት ምንነትና በኢትዮጵያ ምን እንደሚመስል፣ እንዲሁም በፍትህ ተደራሽነትና ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃትን መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው። በመድረኩም ከህግና ፍትህ ጋር በቅንጅት ከሚሰሩ በተለይም ከህግ፣ ፍትህ፣ ፖሊስ፣ ሴቶችና ህጻናት እና ሌሎች ተያያዥ ሴክተሮች የተወጣጡ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
ይህ ፕሮጀክት «Building Adaptive Resilience For People Affected By Conflict And Climate Crises Focusing On Youth In South Ethiopia» በሚል ርዕስ እየተከናወነ ይገኛል። በተለይም ለሴቶች፣ ወጣቶችና ሌሎች ተጎጂ የማህበረሰብ ክፍሎች ጥበቃ እንዲጠናከር ማስቻል እና የፍትህ ተደራሽነት ላይ መስራት የፕሮጀክቱ ዋነኛ ዓላማ እንደሆነ ተገልጿል። በተጨማሪም ዳሰነች ወረዳ፣ ካራት ዙሪያ ወረዳ፣ ሰገን ዙሪያ ወረዳ እና የአርባ ምንጭ ከተማ ፕሮጀክቱ ታቅፈው ስራው እየተከናወነባቸው ያሉ አካባቢዎች መሆናቸው ተጠቅሷል።
በመርሃ ግብሩ የሰገን ዙሪያ ወረዳ ም/አስተዳዳሪ አቶ ከበደ ገኔ በመክፈቻ ንግግራቸው ስልጠናውን ያዘጋጁትን የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ህግ ትምህርት ቤት መምህራን አመስግነዋል። ስልጠናው በአካባቢያቸው ያሉ ችግሮችን ለመፍታት አስፈላጊ መሆኑን በመግለፅ፣ ተሳታፊዎች ለስልጠናው ትኩረት በመስጠትና ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር እንዲቀይሩት አሳስበዋል። ይህ እውቀት ወደ ታች ወደ ማህበረሰቡ ወርዶ ውጤታማ ስራ መስራት የሚያስችላቸው እንዲሆንም ተመኝተዋል።
በመቀጠልም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ህግ ትምህርት ቤት መምህርትና የስልጠናው አስተባባሪ ማህሌት ደመቀ ስልጠናው በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ በአስዴፖ ሀገር በቀል ድርጅት እና በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) ትብብር እንዲሁም ከኮሪያ መንግስት ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (KOICA) በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የሚከናወን መሆኑን ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ ከፍትህ ስርዓቱ ጋር በቅንጅት ከሚሰሩ ቢሮዎች ጋር አብሮ የሚሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ በተለይም ጾታን መሰረት ላደረገ ጥቃት ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችና ህጻናትን መደገፍ ላይ ያተኮረ መሆኑን አስረድተዋል።
በዕለቱ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ህግ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት ዳኛቸው ወርቁ የቤተሰብና የንብረት ህግ መሰረታዊ ደንቦችን አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል። መምህር ዳኛቸው በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 35 ላይ የሚገኘውን የቤተሰብ ህግ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ያብራሩ ሲሆን፣ በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 40 ላይ ከንብረት ጋር በተያያዘ የሴቶችን መብቶች ከመጠበቅ አንጻር ህጉ የሚለውን ነጥብ በስፋት ዳሰዋል።
በተጨማሪም የኢ-መደበኛ (የአማራጭ) የግጭት አፈታት ስርዓት በኢትዮጵያ ምን እንደሚመስል፣ የባህላዊና ኢ-መደበኛ የግጭት አፈታት ስርዓት ምንነት፣ እና የመደበኛና የባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓት ከሰብአዊ መብት ጋር ያላቸው ቁርኝትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች በሌላኛው የህግ ትምህርት ቤቱ መምህር እንድርያስ በለጠ ገለጻ ተደርጎባቸዋል።
በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ ከቤተሰብና ንብረት ህግ መሰረታዊ ደንቦች እንዲሁም ከግጭት አፈታት ስርዓት ጋር በተያያዘ ከታዳሚዎች ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው ከመድረክ ምላሽና ማብራሪያ ከተሰጠ በኋላ መርሃ ግብሩ ተጠናቋል።
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት

