በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከሚገኙ የምርምር ማእከላት መካከል አንዱ የሆነው የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ምርምር ማእከል የወተትና ሥጋ ከብቶች፣ የእንቁላልና ሥጋ ዶሮዎች፣ የዓሣ እና የንብ ዝርያዎችን ማሻሻል፣ ማላመድ፣ ምርትና ምርታማነትን መጨመር እንዲሁም በእንስሳት ጤና እና የተመጣጠነ መኖ አዘገጃጀት ላይ ያተኮሩ ምርምሮችን እየሠራ መሆኑን ገልጿል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ማእከሉ ከተቋቋመ አጭር ጊዜያትን ያስቆጠረ ቢሆንም ለምርምር፣ ለማኅበረሰብ ጉድኝትና ለተማሪዎች የተግባር ልምምድ የሚሆኑ የምርምርና እርባታ ጣቢያዎችን ማቋቋም ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑንና ይህም ለመስኩ ተመራማሪዎች ምቹ የምርምር አካባቢ መፍጠር መቻሉን የምርምር ማእከሉ ዳይሬክተር አቶ እሳቱ በቀለ ተናግረዋል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ በምርምር ማእከሉ 7 ቋሚ ተመራማሪዎችና 6 ቴክኒካል ረዳቶች ያሉ ሲሆን ተመራማሪዎቹ በግብርና ሳይንስ ኮሌጅ እንስሳት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ከሚገኙ ተመራማሪዎች ጋር በመሆን በወተትና ሥጋ ከብቶች፣ በእንቁላልና ሥጋ ዶሮዎች፣ ዓሣና ንብ ዝርያና ምርት ማሻሻል፣ የተመጣጠነ መኖ አዘገጃጀት እንዲሁም በእንስሳት ጤና ላይ ያተኮሩ የምርምር ሥራዎችን እየሠሩ ነው፡፡

ማእከሉ በቆላውም ሆነ በደጋው አካባቢ ተስማሚና ምርታማ አዳዲስ የእንስሳት ዝርያዎችን ለማላመድና ለማውጣት እዲሁም ለዶሮና ለሌሎች እንስሳት የሚውል አዲስ መኖ ለማበልጸግ በትኩረት እየሠራ ሲሆን ከቆላማ አካባቢዎች ባሻገር በደጋማ ስፍራዎችም የደጋ ዓሣ እርባታና ሠርቶ ማሳያ ጣቢያ በማቋቋም ሥራ ለመጀመር ዝግጅት መጨረሱን አውስተዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር የምርምር ማእከሉ ለምርምርና ተያያዥ ሥራዎች በቅርቡ ባቋቋማቸው የምርምር ጣቢያዎች ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ከዶሮ፣ እንቁላልና ወተት ሽያጭ ለዩኒቨርሲቲው ከአምስት ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ያስገኘ ሲሆን ይህም ዘርፉ ከምርምር፣ መማር ማስተማርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ሥራዎች ባሻገር ለዩኒቨርሲቲው ተጨማሪ ገቢ ከማስገኘት አንጻርም ጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የእንስሳትና ዓሣ ዘርፍ እንደ ሀገር ትኩረት የተሰጠው ዘርፍ መሆኑን ያወሱት ዳይሬክተሩ ይህንን የመንግሥት አቅጣጫ በምርምር ለመደገፍና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ ማእከሉ ሰፋፊ ዕቅዶችን ይዞ እየሠራ መሆኑንም  ጠቁመዋል፡፡ 

የዩኒቨርሲቲው የምርምር ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያም በበኩላቸው የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ምርምር ማእከል ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተቋቋመበትን ዓላማ መሠረት ያደረጉ አበረታች ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ማእከሉ የምርምርና የእርባታ ጣቢያዎችን በተለያዩ ስፍራዎች አቋቁሞ እየሠራ ሲሆን በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኘው የግርጫ ዘመናዊ የወተት ላሞች እርባታ ጣቢያን ለአብነት አንስተዋል፡፡ የግርጫ የወተት ላሞች እርባታ ጣቢያ የግንባታ ሥራ በተለያዩ ምክንያቶች የዘገየ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ተስፋዬ አሁን ላይ ለግንባታው መዘግየት ምክንያት የሆኑ ግብአቶች በመሟላታቸው ግንባታው በቅርቡ ይጠናቃቃል ብለዋል፡፡ የወተት ላሞች እርባታ ጣቢያው ሥራ ሲጀምር ከምርምርና ከሠርቶ ማሳያነቱ ባሻገር ፓስቸራይዝድ ወተት ጭምር ለገበያ የሚያቀርብ ሲሆን በአጠቃላይ በምርምር ማእከሉ ከሚገኙ የምርምር መስኮች የሚገኙ እንቁላል፣ ዶሮ፣ ሥጋና ወተት ለዩኒቨርሲቲው ተጨማሪ የገቢ አማራጭ እየሆኑ ነው ብለዋል፡፡ 

በምርምር ማእከሉ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችና ሊሠሩ የታቀዱ ተግባራት ሰፊና በምርምር በጀት ብቻ ሊሸፈኑ የማይችሉ መሆናቸውን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ ተግባራቱን ለማከናወን ተጨማሪ በጀትና ድጋፍ የሚፈልግ በመሆኑ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራር በልዩ ሁኔታ ማእከሉን እንዲደግፍ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት