የዩኒቨርሲቲው የውኃ ቴክኖሎጂና የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች በዋናው ግቢ ለተመደቡ የ2018 ዓ/ም አዲስ ገቢ ተማሪዎች ጥቅምት 17/2018 ዓ/ም የእንኳን ደኅና መጣችሁ አቀባበል አድርገዋል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ ዩኒቨርሲቲው በርካታ ምሁራንን ያፈራ አንጋፋ ተቋም በመሆኑ በዩኒቨርሲቲው የተመደባችሁ ተማሪዎች ዕድለኞች ናችሁ ብለዋል፡፡ ተማሪዎች በቆይታቸው በጥሩ ሥነምግባር ውጤታማ ሆነው ለመውጣት መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡

የተማሪዎች አገልግሎት ዲን አቶ አየልኝ ጎታ ተማሪዎች በሥራ ክፍላቸው በኩል የምግብ፣ የመኝታ፣ የጤና እና ሌሎች አገልግሎቶችን እንደሚያገኙ ጠቁመው የተቋሙን ሕግና ደንብ በማክበር መብታቸውን መጠቀምና ግዴታቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎች የሚያጋጥማቸውን ተግዳሮት ለሰላም ፎረም ቀርበው ማማከር እንደሚችሉ ዲኑ አመላክተዋል፡፡

የሬጅስትራርና አልሙናይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ማሌቦ ማንቻ በምዝገባ ሂደት፣ የኮርስ አወሳሰድ፣ መታወቂያ እና SMIS/ኤስ ኤም አይ ኤስ/ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥዋል፡፡ ተማሪዎች ከወዲሁ የምታስመዘግቡት ውጤት ቀጣይ ለምታደርጉት የትምህርት ክፍል ምርጫ ውድድር ጉልህ ድርሻ አለው ያሉት ዶ/ር ማሌቦ የማንበብ ልምድን ማዳበር እንዲሁም እርስ በእርስ በመግባባት ቤተሰባዊ ፍቅርን ማጽናት ይጠበቅባችኋል ብለዋል፡፡

በሬጅስትራርና አልሙናይ ዳይሬክቶሬት ተባባሪ ሬጀስትራር ረ/ፕ ዘውዴ ጃግሬ ተማሪዎች ከአንድ ሴሚስተር በኋላ በሚያደርጉት የትምህርት ክፍል ምርጫ ያላቸውን አቅምንና ዝንባሌ በሚገባ በማጤን መምረጥ እንዳለባቸው ገልጸው ከውጤት ጋር ተያይዞ ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ የተማሪዎች አገልግሎት ም/ዲን ረዳት አቶ ሳተናው ሳንዶ ተማሪዎች በግቢው በሚኖራቸዉ ቆይታ የመጡበትን ዓላማ አሳክተዉ መሄድ ይችሉ ዘንድ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተግባራዊ የሚደረጉ የዲሲፕሊን መመሪያዎች ላይ ሰፋ ያለ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰጥተው መመሪያውን በመተግበር የመልካም ሰብእና ባለቤት እንዲሆኑ መክረዋል፡፡

በተጨማሪም የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዝደንት ተማሪ ሶፎንያስ ፋንታና የሰላም ፎረም ዋና ሰብሳቢ ተማሪ ምንተስኖት በጆ በኅብረቱና በፎረሙ የሚከናወኑ ተግባራት ላይ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን የኢንስቲትዩቶቹ የጋራ ኮርሶች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊዎች እና የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት ባለሙያዎች የሥራ ክፍሎቻቸውን አስመልክቶ ገለጻ አቅርበዋል፡፡

 

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት