በጅማ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት በጅማ፣ አርባ ምንጭ ፣ አርሲ እና ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲዎች በመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና አገልግሎት መስጫ ተቋማት በአእምሮ ጤና ሕክምና አገልግሎት ላይ የሚስተዋለውን የባለሙያዎች እጥረት ለመቅረፍ ያለመ ፕሮጀክት ተግባራዊ መሆን ጀምሯል::ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
ፕሮጀክቱ " UK Department of Health & Social Care" በ "Global Health Partnership" በኩል ባደረገው የገንዘብ ድጋፍ ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን እንግሊዝ ሀገር የሚገኘው "Warwick" ዩኒቨርሲቲ እና ጅማ ዩኒቨርሲቲ በዋና እና በተባባሪ መሪነት ፕሮጀክቱን ይመራሉ። የዚሁ ፕሮጀክት አካል የሆነ "Mental Health Gap Action Training" በሚል ርእስ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለተወጣጡ መምህራን ሥልጠናም ተሰጥቷል።
ከጅማ ዩኒቨርሲቲ የመጡት የፕሮጀክቱ ተባባሪ ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ቢኒያም ግርማ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት የአዕምሮ ጤና ባለሙያዎች ከፍተኛ እጥረት መኖሩን ገልጸው ይህንን ችግር ለመቅረፍ የዓለም ጤና ድርጅት የአዕምሮ ጤና ክፍተት የድርጊት መርሃ ግብር መመርያ /Mental Health Gap Action Intervention Guide / የተሰኘ በታዳጊ ሀገራት ተግባራዊ የሚሆን ፕሮግራም ዘርግቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ይህ ፕሮግራም በዋናነት " Task Shifting/Sharing " የተሰኘ ስትራቴጂን የሚጠቅም ሲሆን ይህም ከአዕምሮ ጤና ውጪ ያሉ ሌሎች የጤና ባለሙያዎችን በማስልጠን የአዕምሮ ጤና ምርመራና ሕክምና እንዲሰጡ በማድረግ በዘርፉ ላይ የሚስተዋለውን ክፍተት ለመሙላት የሚሰራ ነው ብለዋል።
ይሄው ስትራቴጂ በሀገራችን በሥራ ላይ የሚገኙ የጤናና ሕክምና ባለሙያዎችን በማሰልጠን ተግባራዊ ሲሆን መቆየቱን የገለጹት ተመራማሪው አዲስ የተጀመረው ፕሮጀከት የአዕምሮ ጤና ክፍተት የድርጊት መርሃ ግብር ሥልጠናው በዩኒቨርሲቲዎች በቅድመ አገልግሎት ሥልጠና ላይ ለሚገኙ ተማሪዎች በመስጠት ላይ አተኩሮ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ሥርዓተ ትምህርቶችን በመገምገም የኣንላይን ኮርስ በማዘጋጀት ለተማሪዎች ሥልጠና የሚሰጥ ሲሆን ይህም ተማሪዎች ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ሥራ ሲገቡ ያለምንም ተጨማሪ ሥልጠና የአዕምሮ ጤና ሕክምና አገልግሎት በመስጠት የበኩላቸውን እንዲወጡ ያደርጋል።
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ሐኪምና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ታዲዮስ ኃይሉ ፕሮጀክቱ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በቅርቡ ምክክር ተደርጎ በይፋ ሥራ መጀመሩን አስታውሰው አሁን ላይ ከሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከሚገኙ አራት ትምህርት ክፍሎች ማለትም ከሕክምና ት/ቤት፣ ከነርሲንግ ፣ ኮሚድዋይፈሪ እና ከጤና መኮንን ለተወጣጡ መምህራን ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል። ሥልጠናው በዋናነት የአዕምሮ ጤና ክፍተት የድርጊት መርሃ ግብርን በማስገንዘብና ባሉን ሥርዓተ ትምህርቶችና ኮርሶች ውስጥ ኘሮግራሙን በማካተት ምሩቃኖቻችን በዚሁ መርሃ ግብር የተቃኙ እንዲሆኑና የአዕምሮ ጤና ሐኪም በሌለባቸው ተቋማት አገልግሎቱን እንዲሰጡ ለማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይ መርሃ ግብሩን በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዴት ማካተት ይቻላል የሚለው ጉዳይ በትኩረት ይሰራበታል ያሉት ዶ/ር ታዲዮስ መርሃ ግብሩን በዘላቂነት በሥርዓተ ትምህርቶች ውስጥ እንዲካተቱ ለማድረግ የተለያዩ አማራጮች ተዘጋጅተዋልም ብለዋል። አሁን ላይ በአራቱ ዩኒቨርሲቲዎች ተግባራዊ የሚሆነው የሙከራ ሥራ መሆኑን የጠቆሙት አስተባባሪው የሙከራ ሥራው ውጤተማነቱ ተፈትሾ በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግርዋል። በፕሮጀክቱ የሙከራ ምዕራፍም በአራቱ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ 60 መምህራንና 450 ተማሪዎች ሥልጠና እንደሚወስዱ ዶ/ር ታዲዮስ አውስተዋል።
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት