በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባሉ አራት ዩኒቨርሲቲዎች ማለትም አርባ ምንጭ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ዲላ እና ጂንካ ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ የሚመራው ‹‹Migration Dynamics›› የትብብር ፕሮጀክት ያለበትን ደረጃ፣ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶች እና ቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በተመለከተ ከአራቱም ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ምክትል ፕሬዝደንቶች፣ የምርምር ዳይሬክተሮች፣ የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎችና ዋና ተመራማሪዎች በተገኙበት ሐምሌ 7/2017 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ውይይት ተካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደገለጹት የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ የፍልሰት አጠቃላይ አሁናዊ ክልላዊ ሁኔታ ምን ይመስላል የሚለውን ማጥናትና ለችግሮቹ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለፖሊሲ ግብዓት እንዲሆኑ ማሳየት ነው፡፡ በውይይቱ ፕሮጀክቱ ያለበትን ደረጃ በመገምገም ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶች እና ቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ የጋራ ምክክር መደረጉን ም/ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡

የዲላ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ሀብታሙ ተመስገን በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ያለበት ደረጃ፣ ቀጣይ አቅጣጫዎችና ወደ ተግባር ለማውረድ ተግዳሮት በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ውይይት መደረጉን ገልጸው ለፕሮጀክቱ ተግዳሮት የሆኑ ምክንያቶች ላይ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ መስመር ማስያዝና ችግሮችን መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዘውድነህ ቶማስ ፕሮጀክቱን ያስጀመሩና ለዚህ ደረጃ እንዲበቃ ያደረጉ አካላትን አመስግነው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲ በክልሉ መገኘቱና ብቁ ተመራማሪዎችን መያዙ ትልቅ ዕድል መሆኑንና ለፕሮጀክቱ ስኬት በጋራ በቅርበት እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ጉዳዮች  ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም ስለ ዩኒቨርሲቲው አጠቃላይ የምርምር ሥራ ውጤቶችን በተመለከተ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን በተመሳሳይ በክልሉ የፕሮጀክት ዋና አስተባባሪ ዶ/ር ታገሰ አቦ ፕሮጀክቱ ያለበትን ደረጃ የውይይት መነሻ ሃሳብ አቅርበዋል፡፡

በመጨረሻም የፕሮጀክቱን አመራር ሂደት እና የእያንዳንዱን ተቋም ድርሻ አስመልክቶ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡  

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት