አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከአርባ ምንጭ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ከአርባ ምንጭ ከተማ ለተወጣጡ ወጣቶች ከመስከረም 11-15/2017 ዓ.ም ለ5 ተከታታይ ቀናት የቆየ የሰብእና ግንባታ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
ማንነትን ባለማወቅ የሚመጡ ቀውሶች፣ ዓላማና ራእይን ማጎልበት፣ በራስ ላይ ለውጥን ማምጣት፣ የሱስ አስከፊነትና መዘዞቹ፣ ለውጥና የለውጥ ባህርያት እንዲሁም ከውድቀት መነሳት ሥልጠናው ትኩረት ካደረገባቸው ጉዳዮች መካከል ናቸው፡፡
የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት በኃይሉ መርደኪዮስ (ተ/ባ ፕሮፌሰር) ሠልጣኞች ስህተቶቻቸው ላይ በግልጽ መወያየታቸውና ወደ ቀደመ ሕይወታቸው ላለመመለስ መወሰናቸው የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሥልጠናው በአዲስ ማንነትና ሰብእና እንዲመጡ ስለሚያግዛቸው በቀጣይ ሕይወታቸውን ለመቀየር እንዲተጉም አሳስበዋል፡፡
የማኅበረሰብ ጉድኝትና የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ ወጣቶች ሀገርን ሊለውጡ ከሚችሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች መካከል ዋነኞቹ መሆናቸውን ጠቅሰው ሠልጣኞች በሥልጠናው ያገኙትን ግንዛቤ ወደ ሕይወታቸው በማስረጽ ከራሳቸው አልፈው የሌሎችን ሕይወት መቀየር እንደሚጠበቅባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ም/ኃላፊና የወጣት ዘርፍ ኃላፊ አቶ የሱነህ ሳሙኤል በአደንዛዥ ዕፅና በሌሎች ሱሶች ውስጥ ለተዘፈቁ ከ30 በላይ የሚሆኑ ወጣቶች ሥልጠናው መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡
ሥልጠናውን የሰጡት አቶ መርክነህ መኩርያ ሥልጠናው በአደንዛዥ ዕፅና ሱስ ውስጥ ተዘፍቀው የነበሩ ወጣቶች ሰብእናቸውን በመገንባት በራሳቸውና በሌሎች ሕይወት ላይ ለውጥ ማምጣት በሚችሉበት ሁኔታ አመለካከታቸው እንዲቀየርና ግንዛቤያቸው እንዲዳብር ያግዛል ብለዋል፡፡ አቶ መርክነህ ሥልጠናው ተጓዳኝ ሱሶችና ማኅበራዊ ቀውሶችን አስመልክቶ ግንዛቤ በመፍጠር ሠልጣኞች ከሱስ ርቀው ኑሯቸውን በጥሩ ሁኔታ እንዲመሩ መነሳሳትን ይፈጥርላቸዋል ብለዋል፡፡
ሥልጠናው ራሴን በሚገባ እንዳውቅ ረድቶኛል ያለው ከድልፋና ቀበሌ የመጣው ወጣት ታረቀኝ ላቀው በተለያዩ ሱሶች ውስጥ የነበረንን መጥፎ ጊዜ በመተው አዲስ የሕይወት ምዕራፍ ይዘን እንድንቀጥል ያግዘናል ብሏል፡፡ ወደ አካባቢው በመሄድ በመሰል ችግር ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ከችግሩ እንዲወጡ ለማድረግ እንደሚሠራም ቃል ገብቷል፡፡
በመዝጊያ መርሃ ግብሩ ሠልጣኞች ሲፈጽሙ ከነበሩት ያልተገባ ተግባር ለመውጣትና ቀድሞ ወደነበሩበት አስከፊ ሕይወት ላለመመለስ ቃል የገቡ ሲሆን በቀጣይ ሕይወታቸውን በምን ሁኔታ መምራትና ማስቀጠል እንዳለባቸው በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከታዳሚዎች ሃሳቦች ተነስተው ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡
በውይይቱም ወጣቶች ያቋረጡትን ትምህርት መቀጠል፣ በሚፈልጉት የሙያ መስክ መሰማራትና በቴክኒክና ሙያ ትምህርት የሚፈልጉትን መርጠው መማር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ በቀጣይ እንደሚሠራ ተገልጿል፡፡
በሥልጠናው ማጠናቀቂያ ለሥልጠናው ተሳታፊዎች የምስክር ወረቀት የተበረከተ ሲሆን ሠልጣኞችም በዩኒቨርሲቲው የሚገኘውን የአእምሮ ማጎልበትና ተግባቦት ማዕከል (Intelligence Enhancement and Dynamic Communication Center) ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት