የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሁሉ አቀፍ ሴክተር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ከዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ካምፓሶች ለተወጣጡ ተማሪዎች ከሐምሌ 30 - ነሐሴ 3/2016 ዓ/ም የአእምሮ ውቅር ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
በሥልጠናው ማንነትን ማወቅ፣ የመኖር ምክንያትን መለየትና እውን ማድረግ፣ ለውጥና ሕይወትን በደንብ ማየት መቻል፣ ሱስና አደንዛዥ ዕፆች እና ልማዶችን መቀየር የሚሉ ርእሶችን ዳስሷል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ያለ ተማሪ ለሀገር ለውጥ ጉልህ ድርሻ ያለው በመሆኑ ተማሪዎቹ በቀጣይ በሚኖራቸው የሕይወት ዘመን ጤናማ አስተሳሰብና ብሩህ አመለካከት እንዲኖራቸው ታልሞ ሥልጠናው መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ ሥልጠናው በተፈጥሮ የተሰጣቸውን አእምሮ በዕውቀትና በአስተሳሰብ ለመገንባት፣ ራስን በደንብ ለይቶ ለማወቅ፣ ወደ ሥራ ዓለም ሲገቡ የሚያጋጥሟቸውን መስተጋብሮች በቀላሉ ለመዋሐድ እና በጥሩ ሥነ ምግባር ለመታነጽ እንደሚረዳቸውም ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡ ሠልጣኞቹ ያገኙት ዕውቀት ለግል ሕይወታቸው፣ ለማኅበረሰብና ለሀገር እንዲረዳ በተግባር ማዋል እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡
የሁሉ አቀፍ ሴክተር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መርክነህ መኩሪያ ሥልጠናው በዋናነት በሃሳብ የበላይነት የሚያምን እና ያለፈውን አሰላስሎ ነገን መተለም የሚችል ትውልድ ለማፍራት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተለያየ ምክንያት የክረምት ቆይታቸውን በተቋሙ ያደረጉ ተማሪዎች ሥልጠናውን መውሰዳቸውን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ ከመደበኛ ትምህርት በተጨማሪ የሕይወት መምሪያ ክሂሎት እንዲያገኙ የሚረዳቸው መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ መርክነህ ተማሪዎቹ የነገ ሀገርን ለመምራት ትልቅ ድርሻ ያላቸው በመሆኑ እነሱን ማሠልጠን በዜጎች ሰብእናና እሳቤ ላይ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ያስችላል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያ ዓመት ተማሪና የሥልጠናው ተሳታፊ አብርሃም አበበ ሥልጠናው ተማሪዎች መክሊታቸውን እንዲያገኙ የሚረዳ በመሆኑ ከመጀመሪያ ዓመት ጀምሮ ቢሰጥ መልካም መሆኑን ተናግሯል፡፡ መሰል ሥልጠናዎች ዘረኝነትንና ጎሰኝነትን ለማስቀረት ሚናቸው ጉልህ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ጠቁሟል፡፡
ሌላኛው የሥልጠናው ተሳታፊ ተማሪ ጌታዬ ገሬ ራሱን ለማየትና ለወደ ፊት የሕይወት መመሪያ የሚጠቅሙ በርካታ ምክረ ሃሳቦችን እንዳገኘበት ተናግሮ ሥልጠናውን ላዘጋጁ አካላት ምስጋናውን አቅርቧል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት