የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጉድኝትና ዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ከጋሞ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ጋር በመተባበር ከተለያዩ አካባቢዎች ለተወጣጡ ወጣቶች ከጥር 19-23/2017 ዓ/ም የሰብእና ልኅቀት ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ተወካይና የአካዳሚክ ጉ/ም ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር ቦጋለ ገ/ማርያም ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ መስኮች ብቁ ምሁራንን ከማፍራት ጎን ለጎን ለሀገር እድገት መሠረት የሆኑ ወጣቶችን በመልካም ሰብእና ለመገንባት ሰፊ ሥራዎች እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ የወጣቶችን አመለካከት መቀየርና በመልካም ምግባር ማነጽ አንድ ጊዜ ተሠርቶ የሚቆም አይደለም ያሉት ዶ/ር ኢ/ር ቦጋለ ዩኒቨርሲቲው ቀጣይነት ባለው መልኩ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡

የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ሀገሩን የሚወድ፣ በሥነ ምግባር የታነጸና ሥራ ወዳድ ትውልድ ለማፍራት መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ጠቁመው ዩኒቨርሲቲው እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ለሀገር እድገትና ሥልጣኔ ትልቅ ድርሻ ያለውን ወጣት በዕውቀትና በሥነ ምግባር ገንብቶ ወደ ሥራ ለማስገባት የበኩሉን ድርሻ ሲወጣ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ ስብእናው የተገነባ ወጣት ራሱንም ሀገሩንም ለማሳደግ አቅም ይኖረዋል ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ የወጣቶችን ሰብእና ለመገንባት በቅንጅት ሊሠራ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

የማኅበረሰብ ጉድኝትና ዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ የሰብእና ግንባታ ሥራ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም በስፋት ሲሠራበት የቆየ መሆኑን አስታውሰው መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠቱ በያዝነው ዓመት በቁልፍ ተግባራት አመላካች ዕቅድ/KPI/ ተካትቶ እየተሠራበት ነው ብለዋል፡፡ በሥልጠናው የተሳተፉ ወጣቶች ራሳቸውን ከመቀየር ባሻገር አርአያ መሆንና ለሌሎች ወጣቶች መትረፍ ይጠበቅባቸዋል ያሉት ዶ/ር ቶሌራ የሚገጥሟቸውን ችግሮች በጋራ ለመፍታትም ሆነ ለሌሎች ቀጣይ ሥራዎች ዩኒቨርሲቲው ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የምርምር ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም በበኩላቸው ሀገር ተረካቢ ትውልድ እንዲኖር ተተኪ ወጣቶችን ማፍራት ግድ መሆኑን ተናግረው ዩኒቨርሲቲው በዕውቀት ብቻ ሳይሆን በሥነ ምግባርና በሥነ ልቦና የታነጹ ወጣቶችን በማፍራት ተቋማዊና ሀጋራዊ ኃላፊነቱን በመጣት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ 

የጋሞ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ማዜ ሸቀኔ የወጣቶችን ጉዳይ መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት የሰጠው መሆኑን ጠቅሰው ሥራ ወዳድና ሀገር የሚገነቡ ወጣቶችን ለማፍራት ተቀናጅቶ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ መምሪያው የወጣቶችን አስተሳሰብ ለመቅረጽ በሚያደርገው ጥረት ዩኒቨርሲቲው ቀና ተባባሪ በመሆኑም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ሥልጠናውን የሰጡት አቶ መርክነህ መኩሪያ ወጣቶች የአስተሳሰብና የሰብእና ልኅቀት በማምጣት የሕይወት ትርጉምና የመኖር ዓላማን ተረድተው ከተለያዩ ሱሶች በመላቀቅ ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውን ብሎም ሀገርን የሚጠቅሙ ዜጎች እንዲሆኑ በማለም ሥልጠናው መጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ የሕይወት ትርጉምን መረዳት፣ ማንነትና የሚኖሩበትን ምክንያት ማወቅ፣ የመኖር ዓላማን እውን ማድረግ፣ የሕይወት ጥበባት፣ ሱስና መዘዙ፣ ለውጥ እና ሌሎችምን ጨምሮ ሥልጠናው በዘጠኝ ዋና ዋና ይዘቶች መሰጠቱን የጠቀሱት አሠልጣኙ ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ሥልጠና ወስደው ከተለያዩ ሱሶች በመውጣት ለውጥ ያመጡ ወጣቶች ልምዳቸውን ማጋራታቸውን ገልጸዋል፡፡ ሀገር የታለመውን እድገት እንድታስመዘግብ ለአእምሮ ልማት እኩል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባና ከሱስ የጸዳ ትውልድን ለማፍራት በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ አሠልጣኙ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

ሠልጣኞች በአስተያየታቸው ራሳችንን እንድንፈትሽ፣ የአመለካከት ለውጥ በማምጣት ዓላማ ያለው ሕይወት እንድንመራ እና ከተዘፈቅንበት አስከፊ ሱስ እንድንላቀቅ የረዳን ሥልጠና ነው ብለዋል፡፡ ያገኘነውን ብርሃን ለሌሎች ጓደኞቻችን ማጋራት ይጠበቅብናል ያሉት ሠልጣኞቹ መድረኩን ላመቻቹ አካላት ትልቅ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ሥልጠና ወስደው ለውጥ ያመጡ ወጣቶች ልምዳቸውን ሲያካፍሉም በሱስ ከተጎዱበት ጊዜ በመውጣት የማንንም እጅ ሳይጠብቁና ሥራን ሳይንቁ በመሥራት ራሳቸውን ለውጠው እየኖሩ እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውን እየረዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ መጨረሻ ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ ለአሠልጣኝ መርክነህ መኩሪያና ከዚህ ቀደም በነበሩ መሰል ሥልጠናዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱት የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ የምስጋና ምስክር ወረቀትና ሽልማት አበርክቷል፡፡ 


አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት