በኢፌዴሪ የትምህርት ሚኒስትር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ የተመራ የልኡካን ቡድን ጥቅምት 21/2017 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተገኝቶ የዩኒቨርሲቲውን ማኅበረሰብ አወያይቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ዩኒቨርሲቲዎች የእውነትና የዕውቀት ማዕከላት መሆን ይጠበቅባቸዋል ያሉት ፕ/ር ብርሃኑ ጥራት ያለው ትምህርት ከመስጠት አኳያ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ያለባቸውን ክፍተት በማስወገድ ዓላማቸውን እንዲያሳኩ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሪፎርም እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሊተገበር የታሰበው የዩኒቨርሲቲዎች መሠረታዊ ለውጥ ውጤታማ እንዲሆን ዩኒቨርሲቲዎች ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ እና ቀጣይ እርምጃዎች አስመልክቶ ሃሳብ ለመለዋወጥ የውይይት መድረኩ መዘጋጀቱንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አስተዳደርና ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሰሎሞን አብርሃ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተደረገ ሱፐርቪዥን ግብረመልስና ከኦዲት ግኝት አንጻር ዩኒቨርሲቲዎቻችን እንደ አጠቃላይ እና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ነባራዊ ሁኔታ አስመልክቶ የውይይት መነሻ ሰነድ አቅርበዋል፡፡

መወያያ ሰነዱን ተከትሎ ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የተነሱ ሲሆን በዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት እና በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ልኡካን ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ የመምህራን ደመወዝ፣ የተማሪዎች በመረጡት የትምህርት መስክ ብቻ መመደብና ተማሪ የማያገኙ የትምህርት ክፍሎች መበራከት፣ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ጋር ያለው ግንኙነት፣ የምርምር በጀት አፈጻጸም፣ ዩኒቨርሲቲው ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ያለው ትስስር እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው ራስ አገዝ ለመሆን የሚያደርገው ጉዞ ከተሳታፊዎች ከተነሱት ርእሰ ጉዳዮች መካከል ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ዩኒቨርሲቲው በተሰጠው የተልእኮ ልየታ መሠረት ውጤታማ ሥራ እንዲሠራ እንዲሁም በሂደት ራስ ገዝ ሆኖ እንዲንቀሳቀስ ክፍተቶችን የሚያይበትና የማስተካከያ እርምጃ የሚወስድበት መድረክ መፈጠሩ መልካም መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ፕሬዝደንቱ ከተሳታፊዎች ለቀረቡ ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ለችግሮቹ መፍትሔ በመስጠት የተሰጠውን ተልእኮ ለመፈጸም ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እና ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ጋር በጋራ መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት