ከተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት /UNIDO – United Nations Industrial Development Organization/ እና የኢትዮጵያ ምግብ ቁጥጥር ባለሥልጣን /FSSC – Food Safety System Certification/ ድርጅቶች፣ ከተለያዩ ኢንስቲትዩቶችና ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ባለሙያዎች፣  እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው የምርምር ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና ተመራማሪዎች የሽፈራው /Moringa Nursery Site/ ነርሰሪ ሳይትን ኅዳር 22/2015 ዓ/ም ጎብኝተዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

ከተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት /UNIDO/ የመጡት ዶ/ር ለምለም ሲሳይ የሽፈራውን ጥራት ለማስጠበቅ ከኢትዮጵያ ደረጃ መዳቢዎች ባለሥልጣን፣ ከኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ድርጅት፣ ከኢትዮጵያ ምግብ ቁጥጥር ባለሥልጣን ጋር በመተባበር እንደሚሠሩ ገልፀው በዋናነት የሽፈራውን የምግብ ዋስትና ለጥሬ ምግብ ዋስትና ለማዋል የሚያስችልበትን መንገድ ለማገዝ እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ለምለም አክለውም የሞሪንጋ ነርሳሪ ሳይቱ ቀድሞ ከነበረው ደረጃ እጅግ የተለየና ከፍተኛ ለውጥ የሚታይበት መሆኑን ጠቁመው  በቀጣይ ዩኒቨርሲቲዎችም ሆኑ የምርምርና  የልማት ተቋማት የሚሠሯቸውን ሥራዎች በመናበብ ቢሠሩ ሀብት እንዳይባክን እንዲሁም ሥራዎችን በመደጋገፍ ለመሥራት ብዙ ዕድል እንዳለው ማስተዋል መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ከኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የመጡት ዶ/ር እንዳለ አማረ በዩኒቨርሲቲው የሞሪንጋ ነርሰሪ ሳይት ከ50 በላይ የሞሪንጋ ዝርያዎች ተሰብስበው እየተሠራባቸው መሆኑ ጥሩ ግብዓት እንደሚሆናቸውም ገልፀው ኢንስቲትዩቱ የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት  ጋር በሚሠሯቸው ሥራዎችም እንደ ሀገር አቀፍ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በአፍሪካ፣ በምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የምግብ ላቦራቶሪ ማዕከል ሆኖ ተመርጧል ብለዋል፡፡  ለጤና ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ነገር ግን በሚፈለገው ደረጃ ያልተጠቀምንባቸው ብዙ የምግብ ዓይነቶች እንዳሉና ከነዚህም መካከል አንዱ ሞሪንጋ መሆኑን ዶ/ር እንዳለ ገልጸው ይህንንም ከዩኒቨርሲቲው የምርምር ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክቶሬት ጋር በማስተሳሰር በቀጣይ ሊሠሩበት ማሰባቸውንና ዝርያዎቹ ለጤና ያላቸውን ጠቀሜታ በመገምገም ከተሰበሰቡት 50 ዝርያዎች የተሻለውን በመምረጥ ለምግብ የሚውልበትን ሁኔታም እንደሚያመቻቹ ገልፀዋል፡፡

ዶ/ር እንዳለ አክለውም ሞሪንጋ ለሕፃናት ምግብነት እንዲውል በምርምር ደረጃ አልቆ ወደ ማኅበረሰቡ ማውረድ ብቻ እንደቀረውም ጠቁመዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የብዝሃ ሕይወት ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ሽቴ ጋተው ዩኒቨርሲቲው ከጋሞ ዞንና ከተለያዩ ደቡብ ክልሎች 50 የሞሪንጋ ዝርያዎችን ሰብስቦ ምርምር እያካሄደባቸው መሆኑን በመግለጽ በቀጣይ እስከ መድኃኒት ቅመማ ድረስ ለማካሄድ ከዩኒቨርሲቲው ጋር መሥራት የሚፈልጉ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ተቋሞች ካሉ ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪ ረ/ፕ አዘነ ተስፋዬ  እንደገለጹት የሞሪንጋ ተክል እንደየአካባቢው በባህላዊ መንገድ ለተለያዩ በሽታዎች በመድኃኒትነት እንደሚውል ተናግረው ይህንንም ደረጃውን በጠበቀና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ ለማዋል በምርምር ተደግፎ እየተሠራበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡  እንደ ረ/ፕ አዘነ ከዚህ ቀደም በዩኒቨርሲቲው በተጠናው ጥናት መሠረት በጋሞ ዞን አካባቢ ወንዴና ሴቴ የሚባሉ ሁለት ዓይነት የሞሪንጋ ዝርያዎች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡  

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት