የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት በ2018 የትምህርት ዘመን በዩኒቨርሲቲው አዲስ ለተመደቡ ተማሪዎች በዋናው ግቢ፣ ኩልፎ፣ አባያና ጫሞ ካምፓሶች ጥቅምት 21/2018 ዓ/ም የሕይወት ክሂሎት ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
ሥልጠናው በዩኒቨርሲቲው የሥነ ትምህርትና ሥነ ባሕርይ ት/ቤት እና በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህራን የተሰጠ ሲሆን ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ከቤተሰብ ርቀው እንደመኖራቸው ማንኛውንም ውሳኔ በጥንቃቄና ሚዛናዊ ሆነው እንዲወስኑ፣ በአቻ ግፊትና በሌሎች ተጽዕኖዎች ምክንያት ወደ ሱስ እንዳይገቡ እንዲሁም ራሳቸውን ከኤች አይ ቪ/ ኤድስና ሌሎች የአባላዘር በሽታዎች እንዲጠብቁ ሥልጠናው የሚያግዛቸው መሆኑን የጽ/ቤቱ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ሠናይት ሳህሌ ገልጸዋል፡፡ አክለውም የሕይወት ክሂሎት ሥልጠና ለተማሪዎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ፣ ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ፣ መልካም ተግባቦትን እንዲፈጥሩ እንዲሁም በራሳቸው የሚተማመኑ እንዲሆኑ የሚረዳ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የሳይኮሎጂ ት/ክፍል መምህር አሠልጣኝ ነብዩ በድሉ የሕይወት ክሂሎት ሥልጠና የተለያዩ የዕውቀት እና የክሂሎት መረጃዎችን ለወጣቶች በማስተላለፍ መልካም እና ጤናማ ማኅበራዊ ግንኙነት እንዲኖራቸው፣ አዎንታዊ አመለካከት እንዲያዳብሩና ባለ ራእይ እንዲሆኑ፣ በወቅታዊ መረጃ፣ ዕውቀትና ክሂሎት ታግዘው ጥሩ መወሰን እንዲችሉ እንዲሁም ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችንና ፈተናዎችን አርቀው በማሰብ እና ክሂሎታቸውን በመጠቀም መቋቋምና ማሸነፍ እንዲችሉ የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳዩች አካቶ ትግበራ ቡድን መሪ አቶ አብዮት በላይነህ ሥልጠናው የአቻ ግፊትን ለመቋቋም፣ የአቻ ለአቻ ምክክር ለመስጠት እንዲሁም ከኤች አይ ቪ/ኤድስና ከአደንዛዥ ዕፆች ራስን ለመጠበቅ የሚያስችል መሆኑን እና ከዚህ ቀደም ለሴት ተማሪዎች ብቻ ይሰጥ እንደነበር ጠቅሰው በአጠቃላይ አዲስ ገቢ ተማሪዎች ሰዓታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙና በአእምሮ ዝግጁ ሆነው በጋራ የተሻለ ለውጥ እንዲያመጡ ለሁሉም አዲስ ገቢ ተማሪዎች መሰጠቱን አብራርተዋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት

