አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ‹‹ኀብረ-ብሔራዊ አንድነት ለዘላቂ ሠላም›› በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን 17ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን ኅዳር 23/2015 ዓ/ም በፓናል ውይይት አክብሯል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን ስናከብር የሀገራችን ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በማንነታቸው በመኩራት ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውንና ሌሎችንም ማኅበራዊ  እሴቶቻቸውን በማሳደግ፣ በመከባበር ላይ የተመሠረተ ጠንካራ አንድነት በመፍጠር፣ በኢኮኖሚ የበለጸገች ሀገር ለመሆን የሚደረገውን ጉዞ የተሻለ ጎዳና የማድረግ እሳቤን ለማጎልበት መሆን አለበት ብለዋል፡፡ ሀገራችን ያላትን የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ፀጋዎችና ምቹ የአየር ንብረት ጨምሮ በተገቢው ሁኔታና ደረጃ በመጠቀም የሀገሪቱን ልማትና የሕዝቦቿን ተጠቃሚነት ከፍ ማድረግ ሁልጊዜም በፊታችን ላይ አስቀምጠን የምንሠራበት አጀንዳ ሊሆን ይገባል ያሉት ፕሬዝደንቱ መሰል ፓናል ውይይቶች ኅብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን በማጠናከር ዘላቂ ሠላምን ለማስፈን የሚያግዙ ሃሳቦች የሚንሸራሸሩበትና የተሻለ ግንዛቤ የሚፈጠርበት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የሕግ ት/ቤት መምህር አቶ ደረጀ ማሞ የፌዴራሊዝም ምንነትና መሠረታዊ ባህሪያት አስመልክቶ ባቀረቡት የመነሻ ጽሑፍ ፌዴራሊዝም ሕዝቦች በእኩልነት መርህ፣ በመነጋገርና በመወያየት በቃል ኪዳን ሠነድ ማሰሪያነት የፖለቲካ ማኅበረሰብን የሚገነቡበት አማራጭ መንገድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡. የጋራ አስተዳደር /Shared Rule/ እና የግል አስተዳደር /Self-Rule/ ሁለቱ መሠረታዊ የፌዴራሊዝም መርሆዎች መሆናቸውን የገለጹት መ/ር ደረጀ ፌዴራሊዝም ብዝኃነትን ለማስተናገድ፣ ሰፊ ገበያና ትልቅ ኢኮኖሚን ለመገንባት፣ ጠንካራ የመከላከያና ደኅንነት ባለቤት ለመሆንና የአምባገነንነት አዝማሚያን ከመከላከል አንፃር ጉልህ ሚና የሚጫወት የመንግሥት አወቃቀር ሥርዓት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የፌዴራሊዝም አስተሳሰብ የሰው ልጆች የግል እና የጋራ ጉዳዩቻቸውን አቻችለዉ አንድ ላይ እንዲኖሩ የሚያስችላቸው በርካታ መሠረታዊ እሴቶችን በውስጡ ያካተተ ጽንሰ ሃሳብ ነው ያሉት የመነሻ ጽሑፍ አቅራቢው በዓለማችን ከሚገኙ ሀገራት መካከል 28ቱ ይህንኑ የመንግሥት አወቃቀር የሚከተሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በማኅበራዊና ሥነ-ሰብ ሳይንስ ኮሌጅ የሥነ-ዜጋና ሥነ-ምግባር ት/ት ክፍል መምህር ዶ/ር ያሲን ሁሴን  በኅብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ሥርዓት ምንነት፣  ባህሪያት እና የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሑፍ ኅብረ-ብሔራዊነት ብዙ ወይም የተለያዩ ብሔሮች በአንድነት በጋራ መኖርን የሚገልፅ ሐረግ ነው፡፡ ይኸውም ኅብረ-ብሔራዊ የሆኑ ማኅበረሰቦችን ለማስተዳደር ብሐሮች በሰፈሩበት ተያያዥ በሆነ መልክዓ ምድር ላይ ራስን ማስተዳደር፣ ማደራጀትና በሀገር ደረጃ በአንድ ሀገራዊ ፌዴራላዊ መንግሥት ማዕቀፍ በጋራ ጉዳዩች ላይ ተሳትፎን ማረጋገጥን መሠረት ያደረገ ፌዴራላዊ አደረጃጃት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይህ የፌዴራላዊ አደረጃጀት ከአደረጃጀቱ ጋር የተያያዙ አከራካሪ የሆኑ ጉዳዩች የሚነሱበት መሆኑን ያወሱት ዶ/ር ያሲን የመንግሥት መፍረስ፣ የፖለቲካ ዋልታ ረገጥነት፣ የውስጥ ህዳጣን ቡድኖች መብቶች አለመከበር ጋር ተያይዞ ችግሮች ይገጥማሉ የሚሉ የንድፈ ሀሳብና አንዳንዴም ከተሞክሮ የሚነሱ ክርክሮች በዘርፉ አጥኚዎች ይቀርባሉ ብለዋል፡፡

የሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር ዕድል በሕገ መንግሥት ደረጃ የተረጋገጠ እና ተግባራዊ መደረግ የተጀመረ መሆኑ፣ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባህላቸውን በተግባር የሚገልጹበት ሕዝባዊ ቦታ ማግኘታቸውና መግለጻቸው እንዲሁም አንዱ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ በሌላው ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ እንዲታወቅና የሀገሪቱ ባህል አንድ አካል መሆኑን እውቅና እንዲያገኝ መደረጉ ሀገራችን ባለፉት ዓመታት ተግባራዊ ባደረገችው የፌዴራል ሥርዓት የተገኙ ትሩፋቶች ሲሆኑ የብሔር መብትንና ሀገራዊ አንድነትን አመጣጥኖ አለማየት፣ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች መበራከት፣ አካባቢያዊ አቅምንና ሀብትን በአንድ ማዕከል የማከማቸት ዝንባሌ መኖር በዚህ ሥርዓት ውስጥ የገጠሙ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ዶ/ር ያሲን በጽሑፋቸው አውስተዋል፡፡ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ የሚያግዙ የጋራ እሴቶችን ለይቶ መገንባት፣ ብዝኃነትን ያከበረ የተሳሰረና የተዋሐደ ማንነት መገንባት፣ በሕዝቦች መካከል መተማመንን የሚፈጥሩ ተግባራትን ማከናወን በቀጣይ ትኩረት ሊሠጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸውንም ምሁሩ ጠቁመዋል፡፡

በቀረቡ የውይይት መነሻ ሀሳቦች ላይ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በተሳታፊዎች ቀርበው ምላሽ የተሰጠባቸው ሲሆን  የጋሞ ዞን ባህላዊ ኪነት ባንድ የተለያዩ የብሔረሰቦች ውዝዋዜና ጣዕመ ዜመዎችን በማሰማት ዕለቱን አድምቋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት