አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ትኩረት የሚሹ ቆላማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማዕከል ከኒዮርክ እና ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር በኮንሶ ዞን ኮልሜ ወረዳ የቆዳ ስር ፈንገስ/Mycetoma/ በሽታ ጫናና ስርጭትን ለማወቅ የሚያስችል የምርምር ፕሮጀክት ሰኔ 24/2016 ዓ/ም ይፋ አድርጓል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡
“Piloting Integration of Mycetoma Surveillance and Control within Ethiopia’s NTD Program through Sentinel Surveillance and Knowledge Transfer in Koleme Disrict, Konso Zone” በሚል ርዕስ የሚሠራው ፕሮጀክት 10 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ከኒዮርክ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም 300 ሺህ ብር ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተመድቦለታል፡፡
ትኩረት በሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማዕከል ተባባሪ ተመራማሪና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ዓለማየሁ በቀለ እንደገለጹት የቆዳ ስር ፈንገስ/Mycetoma/ በዓለም ጤና ድርጅት ትኩረት ከሚሹ የቆላና ሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች መካከል የተመደበ የቆዳ በሽታ ሲሆን በሽታዉ ዝናብ አጠር፣ ቆላና ሐሩራማ በሆኑ አካባቢዎች በብዛት ይገኛል:: በሽታው ከ70 በሚበልጡ እውን ፈንገስ /Eumycetes/ እና ቅርፀ ብዙ ባክቴሪያ /Actinomycetes/ አማካኝነት የሚከሰት መሆኑን የገለጹት ተመራማሪው ጫማ አለመጫማት፣ ባዶ እግር መሄድ፣ ነጠላ ጫማ ብቻ መጫማትና በእሾህ፣ እንጨት ወይም ጋሬጣ መወጋት ለበሽታው የሚዳርጉ ምክንያቶች ናቸው፡፡ በአብዛኛው እግርን የሚያጠቃው በሽታው በየትኛውም የሰውነት አካል ላይ ሊከሰት የሚችልና በሕሙማኑ ላይ ከፍተኛ የሆነ አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊና ማኅበራዊ ቀውስ ሊፈጥር የሚችል መሆኑን አቶ ዓለማየሁ አክለዋል ።
በኢትዮጵያ የቆዳ ስር ፈንገስ ያለው ስርጭትና ጫና በውል አልተጠናም ያሉት ተመራማሪው በፕሮጀክቱ በተመረጠው ኮንሶ ዞን ኮልሜ ወረዳ የቅኝት/Surveillance/ ሥራ በማከናወን የበሽታውን ስርጭትና ጫናን ማወቅ በሂደትም በሽታው እንደ ሀገር ትኩረት ከሚሹ ሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች ፕሮግራም ዝርዝር ውስጥ እንዲካተትና አስፈላጊውን የግብዓት አቅርቦት እንዲኖረው ማስቻል የፕሮጀክቱ ዋነኛ ግብ መሆኑን አቶ ዓለማየሁ ገልጸዋል፡፡ በፕሮጀክቱ ከቆዳ ስር ፈንገስ ባሻገር ሌሎች በቆዳ ላይ የሚከሰቱ የቆላማ አካባቢ በሽታዎችን ስርጭትና ጫናን የመለየት ሥራ በተቀናጀ መንገድ የሚሠራ መሆኑንም ተመራማሪው ተናግረዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በምርምር ተደግፈው የሚወጡ ሳይንሳዊ መረጃዎችና ዕውቀቶች በበሽታዎች መከላከልና ስርጭት መቀነስ ሂደት ወስጥ ጉልህ ሚና እንደሚጫወቱ ተናግረዋል፡፡ የበሽታ ቅኝት ሥራ በጤና ሥርዓት ውስጥ የበሽታን ጫናና ጉዳት በመለየት ረገድ ወሳኝ ሚና የሚጫወት መሆኑን ያወሱት ም/ፕሬዝደንቱ ይፋ በተደረገው ፕሮጀክት የሚሠሩ የቅኝት ሥራዎች እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል ለሚሠሩ ቀጣይ ሥራዎችና ፖሊሲዎች እንደ ግብዓት ሆነው የሚያገለግሉ በመሆኑ ፋይዳው ዘርፈ ብዙ ነው ብለዋል፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት ጤና ቢሮ የበሽታ መከላከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ኩሲያ እንደተናገሩት በሀገራችን 12 ትኩረት የሚሹ ቆላማ አካባቢ በሽታዎች ተመዝግበውና በፕሮግራም ታቅፈው የማኅበረሰቡ የጤና ችግር የማይሆኑበት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቆዳ ስር ፈንገስ/Mycetoma/ በሽታን ስርጭትና ጫናን ለማወቅ የጀመረው ፕሮጀክት ጠቀሜታው ዘርፈ ብዙ ሲሆን በተለይ በጥናቱ የሚገኙ መረጃዎች እንደ ሀገር በበሽታው ላይ ያለውን ሳይንሳዊ የመረጃ ክፍተት የሚሞላ ነው ብለዋል፡፡ የዚህ ፕሮጀክት የመጨረሻ ውጤት የቆዳ ስር ፈንገስ በጤናው ሥርዓት ውስጥም ሆነ ከ12ቱ በሽታዎች ዝርዝር ውስጥ ተካቶ ተገቢው ሥራ እንዲሠራና በበሽታው የተያዙ ሰዎች ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኙ የሚያግዝ በመሆኑ የክልሉ ጤና ቢሮ ለምርምር ፕሮጀክቱ ስኬት የሚጠበቅበትን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በፕሮጀክት ማብሰሪያ ፕሮግራሙ ላይ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ፣ የኮንሶ ዞን፣ የኮልሜ ወረዳ የጤና ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች፣ ከአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል፣ ከካራት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፣ ኮልሜ ወረዳ ከሚገኙ ጤና ጣቢያዎችና ጤና ኬላዎች የተወጣጡ ባለሙያዎች የተገኙ ሲሆን በሥራው ላይ በቀጥታ ለሚሳተፉ የጤና ባለሙያዎችም በበሽታው ምንነት፣ ምልክቶችና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ለ3 ቀናት የሚቆይ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት