የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማዕከል ከባሕር ዳር እና መቐለ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ‹‹Drugs for Neglected Diseases initiative (DNDi)›› ከተሰኘ ዓለም አቀፍ ተቋም በተገኘ 167 ሺህ የአሜሪካን ዶላር በጀት በሀገር አቀፍ ደረጃ የቆዳ ስር ፈንገስ/Mycetoma/ በሽታን ጫናና ስርጭት ለማወቅ የሚያስችል የትብብር ምርምር ፕሮጀክት እየሠራ መሆኑን ገልጿል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የምርምር ሥራውን ለማስጀመር ከአራቱ ክልሎች ተወጣጥተው በምርምር ሥራው በመረጃ ሰብሳቢነት ለሚሳተፉ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች፣ የጤና መኮንኖች፣ ጠቅላላ ሐኪሞችና ተመራማሪዎች የልየታና መረጃ የመሰብሰብ ሥራን በአግባቡ እንዲሠሩ የሚያስችል ሥልጠና በአርባ ምንጭ፣ መቐሌና ደሴ ከተሞች መሰጠቱም ታውቋል፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ትኩረት የሚሹ የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማዕከል ዋና ተመራማሪና የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ ፕ/ር ወንድማገኝ እምቢያለ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ በዋናነት በአርባ ምንጭ፣ ባሕር ዳር እና መቐሌ ዩኒቨርሲቲዎች በትብብር የሚሠራ ሲሆን ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ ‹‹Drugs for Neglected Diseases initiative (DNDi)›› ከተሰኘ ዓለም አቀፍ ተቋም የተገኘ ነው፡፡ የምርምር ፕሮጀክቱ በአራት የኢትዮጵያ ክልሎች ማለትም በትግራይ፣ አፋር፣ አማራ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች በሚገኙ ስምንት ወረዳዎች ወካይ ናሙና ተወስዶ የቆዳ ስር ፈንገስ/Mycetoma/ በሽታን ጫናና ስርጭት ማወቅና መሰነድ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ መሆኑን ዋና ተመራማሪው አመላክተዋል፡፡
የማዕከሉ ተባባሪ ተመራማሪና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ዓለማየሁ በቀለ የቆዳ ስር ፈንገስ/Mycetoma/ በዓለም ጤና ድርጅት ትኩረት ከሚሹ የቆላና ሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች መካከል የተመደበ የቆዳ በሽታ ሲሆን በኢትዮጵያ የሽታውን ስርጭትና ጫና አስመልክቶ በውል የተጠና ጥናት ባለመኖሩ የምርምር ፕሮጀክቱን መሥራት አስፈልጓል ብለዋል፡፡ የበሽታውን ስርጭት፣ በሽታውን የሚስከትሉ ፈንገሶችና ባክቴሪያዎች ዝርያና ዓይነትን መለየት፣ ለበሽታው የሚያጋልጡ ሆኔታዎች እንዲሁም ነባራዊ የበሽታው ምርመራና ሕክምና አሰጣጥ ምን እንደሚመስል ማወቅና በሽታው በሕሙማን ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተጽእኖ መፈተሸ የምርምር ፕሮጀክቱ ዋነኛ ትኩረት መሆኑን ተመራማሪው ተናግረዋል፡፡ ከምርምር ሥራው የሚገኘው ውጤትም እንደ ሀገር ስለ በሽታው ያለውን የመረጃ ክፍተት በመሙላት በሽታውን የመከላከል ሥራው መረጃ ላይ የተመሠረት እንዲሆን እና ለሕክምና የሚያስፈልጉ ግብአቶች አቅርቦት እንዲሟላ ያስችላል ብለዋል፡፡
የቆዳ ስር ፈንገስ /Mycetoma/ በዓለም ጤና ድርጅት ትኩረት ከሚሹ የቆላና ሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች መካከል የተመደበ የቆዳ በሽታ ሲሆን በሽታው ዝናብ አጠር፣ ቆላና ሐሩራማ በሆኑ አካባቢዎች በብዛት ይገኛል:: በሽታው ከ70 በሚበልጡ እውን ፈንገስ /Eumycetes/ እና ቅርፀ ብዙ ባክቴሪያ /Actinomycetes/ አማካኝነት የሚከሰት ሲሆን ባዶ እግር መሄድ፣ ነጠላ ጫማ ብቻ መጫማትና በእሾህ፣ እንጨት ወይም ጋሬጣ መወጋት ለበሽታው የሚዳርጉ ምክንያቶች መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት