አርባ ምንጭ እና ጂንካ ዩኒቨርሲቲዎች ‹‹The Grammar of Ongota: Documentation and Description›› በሚል ርእስ ባለፉት ሦስት ዓመታት ሲያካሂዱት የቆየው የምርምር ፕሮጀክት የጥናት ውጤት ግምገማ (Review) ወርክሾፕ ሐምሌ 19/2017 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
በእለቱ በፕሮጀክቱ የተሠሩ በቋንቋው ተናጋሪ ማኅበረሰቦች ታሪክ፣ ባህላዊ ሕክምና፣ የግጭት አፈታት፣ ቃላዊ ተረኮች፣ የቋንቋ ሰዋሰውና ሌሎች ርእሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ሰባት ጥናቶች ቀርበው ተገምግመዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ የግምገማ አውደ ጥናቶች የምርምርን ጥራትና ተፅዕኖ ለማሳደግ፣ትብብርን ለማጎልበት እና ጠንካራ የአካዳሚክ ማህበረሰብ ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።በአሁኑ ወቅት ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር መሥራት በእጅጉ ይፈለጋል ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ በኦንጎታ ቋንቋ ላይ የተሰራው የምርምር ፕሮጀክት ከጂንካ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር የተሰራ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው የትብብር ሥራ መሆኑን ገልፀዋል። በቅርቡ የተመሰረተው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የትብብር ፎረም ለዚሁ በር መክፈቱን አስታውሰዋል፡፡ ምክትል ፕሬዝደንቱ አያይዘው በቀጣይ ጥናቱን ተመስርተው ሊሰሩ የታሰቡ ተግባራት ግዙፍ ገንዘብ የሚጠይቁ በመሆናቸው ሥራውን ሊያግዙ የሚችሉ አጋር አካላትን የመፈለግ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የምርምር ሥራው ከታየዘለት የጊዜ ሰሌዳ ቀደም ብሎ መጠናቀቁ በሥራው ላይ የተሳተፉ ተመራማሪዎችንና አስተባባሪዎችን ቁርጠኝነትና ትጋት ያሳያል ያሉት ዶ/ር ተክሉ የጥናት ውጤትን በመገምገም ሙያው ድጋፍ ላደረጉ ባለሙያዎችም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በቋንቋና ባህል ዙሪያ በተለይም የመጥፋት አደጋ በተጋረጠባቸው ቋንቋዎችና ባህሎች ላይ ያተኮሩ ጥናቶችን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የጋሞ ዱቡሻን በዩኔስኮ እንዲመዘገብ የሚያስችል ግዙፍ የምርምር ሥራ እየሰራ መሆኑን በንግግራቸው ያነሱት ዶ/ር ተስፋዬ ከጂንካ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን አምስት ተናጋሪዎች ብቻ በቀሩት የኦንጎታ ቋንቋና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የተከናወነው የምርምር ፕሮጀክት ከሀገር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና የሚያሰጥ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ዋና ተመራማሪ ዶ/ር ስንታየሁ ሰሙ ወርክሾፑ የፕሮጀክቱ የመጨረሻ የምርምር ውጤት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በሚገኙበት መድረክ (Dissemination Workshop) ላይ ከመቅረቡ በፊት በተለያዩ የዘርፉ ምሁራን በማስተቸት ተጨመሪ ሃሳቦችንና አስተያየቶችን ለመሰብሰብ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የምርምር ሥራውን ለማከናወን በርካታ አስቸጋሪ ሂደቶች ታልፈዋል ያሉት ዶ/ር ስንታየሁ የማኅበረሰቡን ቋንቋንና ሌሎች እሴቶችን ከመጥፋት ለመታደግ የምርምር ውጤቱ ላይ ተመሥርተው የሚሰሩ የተግባር ሥራዎች በእጅጉ ወሳኝ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት