በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ የሙዝ ግንድን በመጠቀም ለአትክልትና ፍራፍሬ የሚያገለግል ጨዋማ አፈርን ማከም እንዲሁም የምርት መጠንን መጨመር የሚያስችል ተፈጥሯዊ ፈሳሽ ማዳበሪያ በምርምር መገኘቱን ተመራማሪዎች ገልጸዋል፡፡ ለምርምር ሥራው ዩኒቨርሲቲው 1.75 ሚሊየን ብር የመደበ ሲሆን በሥራው ላይ ስድስት ተመራማሪዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ሆርቲካልቸር ት/ክፍል መምህርና የፕሮጀክቱ ዋና ተመራማሪ ዶ/ር ገዛኸኝ ጋሮ እንደገለጹት በአካባቢያችን በተለይ በጫሞና አባያ ሐይቆች አካባቢ ሶዲየም ንጥር ነገር በስፋት አፈር ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ የአፈር ጨዋማነት ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ በመምጣቱና ይህም ምርትን በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ መሆኑ ጥናቱን ለማድረግ አነሳስቷል፡፡ ፈሳሽ ማዳበሪያውን ለመሥራት በዋናነት የሙዝ ግንድን እንደ ግብአት የተጠቀሙ መሆኑን የገለጹት ተመራማሪው ማዳበሪያውን በቤተ ሙከራና በመስክ የሽንኩርት ተክል ላይ በመጠቀም አመርቂ ውጤት ማየት መቻሉን ተናግረዋል፡፡ የምርምር ውጤቱ ጨዋማ አፈርን የማከም አቅም ያለው መሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን ምርትን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምርም አረጋግጠናል ብለዋል፡፡

በምርምር የተገኘው ማዳበሪያ ሙሉ በሙሉ ተፈጥሯዊ ሲሆን ይህም በሰውም ሆነ በተፈጥሮ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት የማያስከትል መሆኑ ግኝቱን ይበልጥ ጠቃሚ እንደሚያደርገው ዶ/ር ገዛኸኝ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የተፈጥሮ ማዳበሪያው በሌሎች ወደ ሀገር በምናስገባቸው ማዳበሪያዎች ውስጥ የሌለውን ፖታስየም̋ የተሰኘ ጠቃሚ ንጥረ ነገር መያዙ የተለየ የሚያደርገው ሲሆን በዚህ ንጥረ ነገር እጥረት ሳቢያ የምርት መቀነስ ለሚያጋጥማቸው አካባቢዎች ሥነ ምኅዳሩን በማስተካከል ምርትና ምርታማነትን እንዲጨምር የሚያግዝ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ ማዳበሪያው በአካባቢው በስፋት ከሚገኝ የሙዝ ግንድ የሚሠራ በመሆኑ አርሶ አደሩ በቀላል ዋጋ ሊያገኘው የሚችል መሆኑንም ተመራማሪው አስረድተዋል፡፡ በቀጣይም ፈጠራውን በአርሶ አደር ማሳዎች ላይ በመሞከር የውጤታማነት ፍተሻ ተደርጎ በስፋት ለማኅበረሰቡ ለማዳረስ እንደሚሠራ ዶ/ር ገዛኻኝ ተናግረዋል፡፡

በፕሮጀክቱ የ2ኛ ዲግሪ ጥናቱን እያከናወነ የሚገኘው ለገሠ ቦዴ በምርምሩ የተገኘው ማዳበሪያ አካባቢንና ተፈጥሮን የማይጎዳ መሆኑ እንዲሁም ማዳበሪያው የሚሠራበት ጥሬ ዕቃ በቀላሉ በአካባቢው መገኘት የሚችል መሆኑ ፈጠራውን በቀላሉ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ለማድረስ ያግዛል ብሏል፡፡ በቀጣይ ቴክኖሎጂውን በስፋት ለማዳረስ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል ሊፈጥር እንደሚችልም ጠቁሟል፡፡ 

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት