የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ካንሰርን ጨምሮ ሌሎች በሽታዎችን መመርመር የሚያስቸል የሥነ-ደዌ (Pathology) ምርመራ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
በሆስፒታሉ የሥነ-ደዌ ስፔሻሊስት ሐኪም ዶ/ር ሚልኪያስ ሚልካ ሥነ-ደዌ ሕክምና ዘርፍ ትኩረቱን ምርመራ ላይ ያደረገ በርከት ያሉ የበሽታ ዓይነቶችን መመርመር የሚያስችል ዘርፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሥነ-ደዌ ምርመራ በዋናነት በሰው ልጅ የውጭና የውስጥ የሰውነት ክፍል ውስጥ ከሚወጡ እብጠቶች፣ እጢዎችና ቁስለቶች ናሙና በመውሰድ በሽታን መለየት የሚያስችል የምርመራ ሂደት መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ሚልኪያስ በዚህም የደም፣ የቆዳና የጡት ካንሰርን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የበሽታ ዓይነቶችን መለየት የሚያስችል አድቫንስድ የምርመራ ሥራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሆስፒታሉ የተጀመረው አገልግሎት ታካሚዎች ይህን አገልግሎት ለማግኝት አዲስ አበባና ሀዋሳ ድረስ በመሔድ የሚደርስባቸውን የገንዝብና የጊዜ ብክነት የሚያስቀር ሲሆን ከዚህ በፊት የምርመራ ውጤትን ለማግኘት የሚፈጀውን ረዥም ጊዜ የሚያስቀር እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡ የምርምራ አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችል ከሰው ንክኪ ነጻ የሆኑ ዘመናዊ የምርመራ ማሽኖችንና ሦስት የሥነ ደዌ ስፔሻሊስት ሐኪሞችን ጨምሮ ሌሎች በዘርፉ የሠለጠኑ ባለሙያዎች ዝግጁ ሆነዋል፡፡ ሆስፒታሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ የአስክሬን ምርመራ የ‹Forensic Pathology› አገልግሎት ለመጀመር ዝግጅት እያደረገም ይገኛል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት

