አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አውስትራልያ ሀገር ከሚገኘው "Menzies School of Health Research " ከተሰኘ የምርምር ተቋም እና ከአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ጋር በተመተባበር "Effectiveness of Novel Approaches to Radical Cure With Tafenoquine and Primaquine - a Randomized Controlled Trial in P. Vivax Patients" በሚል ርእስ በኢትዮጵያ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ካምቦዲያና ፓኪስታን ሲደረግ የነበረውን የመድኃኒት ሙከራ የምርምር ውጤት የምርምሩ ተሳታፈዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ሰኔ 26, 2017 ዓ/ም ይፋ አድርጓል።ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጥናትና ምርምር ኮርፖሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ዘርይሁን ዘርዶ ምርምር ከዩኒቨርሲቲው መሠረታዊ ተልዕኮዎች መካከል ዋነኛው መሆኑን ገልጸው ተቋሙ ምርምርን መሠረት ያደረጉ የተለያዩ የማኅበረሰብ ጉድኝት ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከሕትመት ባሻገር የምርምር ውጤቶችን በዚህ ልክ ለምርምሩ ተሳታፊዎች ማሳወቅ የሚበረታታ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ዘርይሁን አስቸጋሪ ባህሪ ባለው የቫይቫክስ ወባ ላይ የተካሄደው የመድኃኒት ሙከራ ጥናት በእጅጉ ጠቃሚ ፣ ለመንግሥት የፖሊሲ ግብአት የሚሆን ለሌሎች መሰል ምርምሮች ግብአትና ልምድ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል መሆኑን አስረድተዋል። ዶ/ር ዘርይሁን ለጥናቱ ተሳታፊዎችና በምርምር ሥራው ለተሳተፉ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በኮሌጁ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ሐኪምና የምርምር ፕሮጀክቱ ዋና ተመራማሪ ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ ቫይቫክስ የተሰኘው ወባ ከደም ውስጥ ባሻገር ከጉበት ውስጥ ረዥም ጊዜ በመቆየት ምቹ ሁኔታ ሲያገኝ በድጋሚ የሚያገረሽ በመሆኑ በሽታው ሁለት ዓይነት ሕክምና ይፈልጋል ብለዋል። ደም ውስጥ ያለውን እንዲሁም ጉበት ውስጥ የተደበቀውን ፓራሳይት ማከምና መግደል በሽታውን ሙሉ በሙሉ ከሰውነት ውስጥ ለማጥፋት የሚደረጉ የሕክምና ሂደቶች መሆናቸውን የገለጹት ዶ/ር ታምሩ ደም ውስጥ ያለውን በሽታ ለማከም ክሎሮኪል እንዲሁም ጉበት ውስጥ ያለውን ፓራሳይት ለማጥፋት "Tafenoquine " እና "Primaquine "
የተሰኙ መድኃነቶች አገልግሎት ላይ ይውላሉ ብለዋል። እነዚህ መድኃኒቶች በ5 ዓይነት መንገድ ወይም አማራጮች ለታማሚዎች ይሰጣሉ ያሉት ዶ/ር ታምሩ "Primaquine " የተሰኘው መድኃኒት በተለያየ ዓይነትና ዶዝ ለሰባትና አስራ አራት ቀናት የሚሰጥ ሲሆን "Tafenoquine" የተሰኘው መድኃኒት ደግሞ አንድ ጊዜ ብቻ የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል። በኢትዮጵያ አሁን ላይ ለ14 ቀናት የሚሰጠው "Primaquine " ብቻ ጉበት ላይ የሚቀመጠውን የቫይቫ ክስ ፓራሳይት ለማጥፋት ጥቅም እየዋለ መሆኑን አስረድተዋል።
የምርምር ሥራው በዋናነት በጉበት ውስጥ ተደብቆ የሚቆየውን ፓራሳየት ለማከም በተለያየ መንገድና መጠን የሚሰጡትን መድኃኒቶች ለታማሚዎች በመስጠትና ክትትል በማድረግ የትኛው መድኃኒትና ዘዴ ይበልጥ ውጤታማ እንደሆነና ዳግም በሽታው በሰውነት ውስጥ ተደብቆ እንዳይነሳ የማድረግ አቅም እንዲሁም አነስተኛ የጎንዮሽ ጉዳት እንዳለው መፈተሸ ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል። በጥናቱ በአራት ሀገራት የሚገኙ 960 ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን 350 ከኢትዮጵያ መሆናቸውን የገለጹት ዶ/ር ታምሩ በጥናቱ በምርምር ሥራው ለተሳተፉ ሰዎች ለ14 እና 7 ቀናት እንዲሁም ለአንድ ጊዜ የሚወሰዱትን መድኃኒቶች በመስጠት የትኛው አማራጭ የተሻለና አነስተኛ የማገርሸት ምጣኔ እንዲሁም የጎንዮሽ ጉዳት ያለው መሆኑ በጥልቀት ተፈትሿል ብለዋል።
ለ14 ቀን የሚሰጠውን "Primaquine " ከወሰዱ ሰዎች መካከል 18.5 ከመቶ፣ ለ7 ቀን የሚሰጠውን "Primaquine " ከወሰዱ ሰዎች መካከል 13 ከመቶ፣ እንዲሁም ለአንድ ጊዜ የሚሰጠውን "Tafenoquine" ከወሰዱ ሰዎች መካከል 12.6 ከመቶ ያህሉ በሽታው ዳግም ያገረሸባቸው መሆኑን የጥናቱ አጠቃላይ ውጤት ያሳያል። የኢትዮጵያን የጥናት ውጤት ለብቻ ያብራሩት ዶ/ር ታምሩ በጥናቱ ከተሳተፉ 350 ሰዎች ለ14 ቀን የሚሰጠውን "Primaquine " ከወሰዱ ሰዎች መካከል 27.3 ከመቶ፣ ለ7 ቀን የሚሰጠውን "Primaquine " ከወሰዱ ሰዎች መካከል 18.4 ከመቶ፣ እንዲሁም ለአንድ ጊዜ የሚሰጠውን "Tafenoquine" ከወሰዱ ሰዎች መካከል 14 ከመቶ ያህሉ በሽታው ደግም ያገረሸባቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም መሠረት ለ14 ቀን ከሚሰጠው "Primaquine " ይልቅ ለ7 ቀን የሚሰጠው እንዲሁም ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚሰጠው "Tafenoquine" በጉበት ውስጥ የሚገኘውን የወባ ፓራሳይት ከማጥፋትና በሽታውን ዳግም የማግረሽት ሁኔታ ከመቀነስ አንጻር የተሻሉ መሆናቸው በጥናቱ መረጋገጡን ዶ/ር ታምሩ አውስተዋል። የተሻለውንና ውጤታማ መድኃኒት ከመለየት ባሻገር መድኃኒቶቹ የሚያስከተሉት የጎንዮሽ ጉዳት በጥልቀት ተፈትሿል ያሉት ዶ/ር ታምሩ በሙከራው ሂደት የከፋና ከሌሎች መድኃኒቶቹ የተለየ የጎንዮሽ ጉዳት አልታየም ብለዋል። ዶ/ር ታምሩ በቀጣይ መሰል ጥናቶች የሚቀጥሉ መሆናቸውንና የዚህን ጥናት ውጤት ለሚመለከታቸው አካላት የማሳወቅ ሥራ በስፋት እንደሚሰራ ተናግረው የምርምር ፕሮጀክቱ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ለተወጡ የጥናቱ ተሳታፈዎችና ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የምርምር ሥራው ሃሳብ አመንጪና ዋና ተመራመሪ ለሆኑት ፕ/ር ካማላ ትሪመር ምስጋና አቅርበዋል።
የጥናቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በዚህ በእጅጉ ጠቃሚና የማኅበረሰብን ችግር በሚፈታ የምርምር ሥራ ላይ በመሳተፈቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል ። በደርሳቸው እጣ መሠረትም ከሶስቱ የመድኃኒት አማራጮች አንዱን ሲወስዱ መቆየታቸውንና በየጊዜው ክትትል ሲደረግላቸው እንደነበርም ገልጸዋል። የጥናቱን የመጨረሻ ውጤት በመስማታቸው መደስታቸውንም የጥናቱ ተሳታፊዎች ገልጸዋል::
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት