በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ የእንስሳት ሳይንስ ት/ክፍል መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ይስሃቅ ከቸሮ የተጻፈ "Scientific Research and Communication: A Guiding Principle and Techniques" የተሰኘ መጽሐፍ ሰኔ 12/2017 ዓ/ም የዩኒቨርሲቲው ሰኔት አባላት በተገኙበት ተመርቋል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማል መጽሐፉ በተማሪዎች ምረቃ ወቅት የተገኘ ትልቅ ስጦታ ከመሆኑም ባሻገር ተቋሙ ካለበት ቁመና አንጻር የሚመጥን ተግባር መሆኑን ገልጸዋል። ዓመቱ የትምህርት ፕሮግራሞች የመከለስና ዕውቅና የማሰጠት እንዲሁም በርካታ የምርምርና ማኀበረሰብ ተኮር ተግባራት የተከናወኑበት መሆኑንም አውስተዋል።
የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በእንኳን ደኅና መጣችሁ ንግግራቸው ‹‹ሃምሳ ዓመትን የሚያስብ ዛፍ ይተክላል! መቶ ዓመትን የሚያስብ መጽሐፍ ይጽፋል!" በማለት መጽሐፉን ለመጻፍ የሚፈጀውን ጊዜና ተግባሩ ከዩኒቨርሲቲው እድገት ጋር አብሮ የሚሄድና ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል። የፕሮፌሰር ይስሃቅ ሥራ በዩኒቨርሲቲው ታሪክ በዚህ ልክ የተመረቀ የመጀመሪው መጽሐፍ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ተክሉ ሥራው ሌሎች መምህራንና ተመራማሪዎችን ለመሰል ተግባር የሚያነሳሳ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ኢ/ር ቦጋለ ገብረማርያም በበኩላቸው ብዙን ጊዜ መመህራን የምርምር ሥነ-ዘዴ ኮርሶችን በሚሰጡ ጊዜ የማጣቀሻ መጽሐፍት ችግር እንደሚገጥማቸው ገልጸው መጽሐፉ ከዚህ አንጻር የሚስተዋለውን ችግር የሚቀርፍ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም መጽሐፉ በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችና መምህራን እንዲሁም ተመራማሪዎች የሚሰሩ የምርምር ሥራዎች ይበልጥ ጥራታቸውን የጠበቁ አንዲሆኑ አጋዥ ሆኖ የሚያገለግል መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ደግፌ አሰፋ ጸሐፊውን አስመልክቶ እንደተናገሩት ፕ/ር ይስሃቅ ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ በ"Animal Sciences" እና ‹‹Range Ecology and Management›› የትምህርት ፕሮግራሞች የመጀመሪያ እና 2ኛ እንዲሁም ከቤልጅየሙ ‹‹Ghent University›› በ"Veterinary Science" (Animal Nutrition & Feed Intervention Technology) የትምህርት ፕሮግራም የሦስተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።
ፕ/ር ይስሃቅ 150 የመጀመሪያ፣ 89 የሁለተኛ አንዲሁም ከ27 በላይ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ያማከሩ ሲሆን ከ75 በላይ የኅትመት ሥራዎችን አሳትመዋል። በተጨማሪም የVLIR-UOS፣ AMU IUC ፕሮጀክት፣ Bright Future in Agricultural-South (BFA-South) እንዲሁም ‹‹International Foundation for Science›› እና በመሰል ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማትና ፕሮጀክቶች ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛሉ።
ፕ/ር ይስሃቅ ከቸሮ መጽሐፉ ለሌሎች መነሻ ሀሳብ ለመስጠት እንዲሁም ለመማር ማስተማር እና ለጥናትና ምርምር እገዛ እንደሚኖረው ታሳቢ በማድረግ መዘጋጀቱን ገልጸዋል። በ30 ምዕራፎች የተከፈለው መጽሐፍ ለማኀበራዊና ተፈጥሮ ሳይንስ የትምህርት ዘርፎች ከማገዙም በተጨማሪ ለሕግ አውጪዎች እና ውጤታማ ጥናትና ምርምር ለሚያከናውኑ አካላት ጠቃሚ መሆኑን ፕሮፌሰሩ አብራርተዋል። መጽሐፉን ለማዘጋጀት ከሁለት ዓመት በላይ የፈጀባቸው መሆኑን የገለጹት ፕ/ር ይስሃቅ መጽሐፉ ታትሞ ለገበያ እንዲበቃ ድጋፍ ላደረጉ አካላት በሙሉ በተለይ ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የመጽሐፉ ገምጋሚ ዶ/ር ቶማስ ቶሮራ በበኩላቸው መጽሐፉ የሁሉን ፕሮግራሞች የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መጽሐፉ ለመምህራን ማስተማሪያ ለተማሪዎች ደግሞ ማጣቀሻ በመሆን ማገልገል የሚችል መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ቶማስ ዘመኑን የዋጀ ስለ ሳይንሳዊ ምርምርና ኮሚዩኒኬሽን የሚያወሳ መጽሐፍ መሆኑንም አክለዋል።
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት